ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36
  37. 37
  38. 38
  39. 39
  40. 40
  41. 41
  42. 42
  43. 43
  44. 44
  45. 45
  46. 46
  47. 47
  48. 48

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ገዢው፣ ሌዋውያኑ፣ ካህናቱ

1. ከዚያም ያ ሰው ለምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በስተ ውጩ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መልሶ አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር።

2. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል፤ መከፈት የለበትም፤ ማንም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔር ገብቶበታልና፤ ተዘግቶ ይኖራል።

3. በእግዚአብሔር ፊት ይበላ ዘንድ በመግቢያው በር ገብቶ ውስጥ ሊቀመጥ የሚችለው ገዡ ራሱ ብቻ ነው፤ በመግቢያው መተላለፊያ በረንዳ እንደ ገባ መውጣትም የሚችለው በዚያው ነው።”

4. ከዚያም ያ ሰው በሰሜኑ በር በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አመጣኝ፤ እኔም ተመለከትሁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞልቶት አየሁ፤ በግንባሬም ተደፋሁ።

5. እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥርዐት የምነግርህን ሁሉ በጥንቃቄ አስተውል፤ በሚገባ አድምጥ፤ ልብም በለው። የቤተ መቅደሱን መግቢያና የመቅደሱን መውጫዎች ሁሉ አስተውል፤

6. ለዐመፀኛው የእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አስጸያፊ ሥራችሁ ከእንግዲህ ያብቃ!

7. ከአስጸያፊ ሥራችሁም ሌላ ምግብ፣ ስብና ደም ስታቀርቡ ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙትን እንግዶች ወደ መቅደሴ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አረከሳችሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አፈረሳችሁ።

8. እናንተ ራሳችሁ ማድረግ የሚገባችሁን ቅዱሳት ሥርዐቶቼን በመፈጸም ፈንታ ባዕዳንን በኀላፊነት በመቅደሴ አስቀመጣችሁ።

9. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ።

10. ‘ “እስራኤል እኔን ከመከተል በራቁ ጊዜ፣ ከእኔ የራቁትና ጣዖቶቻቸውን በመከተል የተቅበዘበዙት ሌዋውያን የኀጢአታቸውን ዕዳ ይሸከማሉ።

11. የቤተ መቅደሱ በር ኀላፊ በመሆንና በእርሱም ውስጥ በማገልገል፣ መቅደሴን ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐርደው ስለ ሕዝቡ ሊሠዉ፣ በፊታቸው ሊቆሙና ሊያገለግሏቸው ይችላሉ።

12. ነገር ግን ሕዝቡን በጣዖቶቻቸው ፊት ስላገለገሏቸውና የእስራኤል ቤት በኀጢአት እንዲወድቅ ስላደረጉ፣ ስለዚህ የኀጢአታቸውን ዋጋ መቀበል እንዳለባቸው እጄን አንሥቼ ምያለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

13. እንደ ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፤ ወይም ቅዱስ ወደ ሆነው ነገሬ ሁሉ፣ ወይም እጅግ ወደ ተቀደሱ መሥዋዕቶቼ አይቀርቡም፤ የአስጸያፊ ድርጊታቸውን ኀፍረት ይሸከማሉ።

14. ያም ሆኖ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲሠሩ፣ በውስጡ የሚከናወኑትንም ሥራዎች ሁሉ እንዲቈጣጠሩ አደርጋቸዋለሁ።

15. ‘ “ነገር ግን እስራኤላውያን ከመንገዴ ስተው በወጡ ጊዜ፣ የመቅደሴን ሥራ በታማኝነት ያከናወኑት የሳዶቅ ዘርና ሌዋውያን የሆኑት፣ በፊቴ ቀርበው ያገለግሉኛል፤ በፊቴ ቆመው የስብና የደም መሥዋዕት ያቀርቡልኛል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16. እነርሱ ብቻ ወደ መቅደሴ ይገባሉ፤ እነርሱ ብቻ በፊቴ ሊያገለግሉ፣ ሥርዐቴንም ሊፈጽሙና ወደ ገበታዬ ሊቀርቡ ይችላሉ።

17. ‘ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሮች ሲገቡ፣ የበፍታ ፈትል ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በሮችም ሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያገለግሉ፣ ከበግ ጠጒር የተሠራ ልብስ አይልበሱ።

18. በራሳቸው ላይ ከበፍታ ፈትል የተሠራ ጥምጥም ያድርጉ፤ እንዲሁም ከበፍታ ፈትል የተሠራ ሱሪ በወገባቸው ላይ ይታጠቁ፤ እንዲያልባቸው የሚያደርግ ማንኛውንም ልብስ አይልበሱ።

19. ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ውጩ አደባባይ ሲወጡ፣ ሲያገለግሉበት የነበረውን ልብስ አውልቀው በተቀደሱት ክፍሎች በመተው ሌሎች ልብሶችን ይልበሱ፤ ይኸውም ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ነው።

20. ‘ “የራሳቸውን ጠጒር አይላጩት፤ ወይም አያርዝሙት፤ ነገር ግን ይከርክሙት።

21. ማንኛውም ካህን ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጣ።

22. መበለቶችን ወይም ፈት ሴቶችን አያግቡ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ዘር የሆኑ ድንግሎችን ወይም የካህናት ሚስቶች የነበሩትን መበለቶች ማግባት ይችላሉ።

23. በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ያለውን ልዩነት ለሕዝቤ ያስተምሩ፤ የረከሰውንና ያልረከሰውን እንዴት እንደሚለዩም ያሳዩአቸው።

24. ‘ “በማንኛውም ክርክር ካህናት ዳኞች ሆነው ያገልግሉ፤ በሥርዐቴም መሠረት ይወስኑ። የተለዩ በዓላቴን የሚመለከቱ ሕጎቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ ይጠብቁ፤ ሰንበታቴንም ቅዱስ አድርገው ይጠብቁ።

25. ‘ “ካህን ወደ ሞተ ሰው ሬሳ በመጠጋት ራሱን አያርክስ፤ ይሁን እንጂ ሟች አባቱ ወይም እናቱ፣ ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ፣ ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ብትሆን፣ ራሱን ማርከስ ይችላል።

26. ከነጻም በኋላ፣ ሰባት ቀን መቈየት አለበት።

27. በመቅደሱ ለማገልገል፣ ወደ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ በሚገባበት ቀን፣ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

28. ‘ “ለካህናቱ ርስታቸው እኔ ብቻ ነኝ፤ በእስራኤል ምንም ዐይነት ርስት አትስጧቸው፤ እኔ ርስታቸው እሆናለሁ።

29. የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕትይበላሉ፤ በእስራኤል ለእግዚአብሔር የተሰጠው ሁሉ የእነርሱ ይሆናል።

30. ከፍሬ በኵራት ምርጥ የሆነው ሁሉ እንዲሁም ከልዩ ስጦታዎቻችሁ የመጀመሪያው ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ ለቤተ ሰዎቻችሁ ሁሉ በረከት እንዲሆን ከምድር የምታገኙትን መብል በኵራት ለእነርሱ ስጧቸው።

31. ካህናት ሞቶ የተገኘውን ወይም በዱር አራዊት የተዘነጠለውን ወፍም ይሁን ሌላ እንስሳ፣ ማንኛውንም ነገር መብላት የለባቸውም።