ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እኛ ብርቱዎች የሆን፣ የደካሞችን ጒድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም።

2. እያንዳንዳችን ባልን ጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል፤

3. ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት።

4. በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።

5. ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤

6. ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።

7. እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።

8. ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደሆነ እነግራችኋለሁና፤

9. እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ለስምህም እዘምራለሁ።”

10. ደግሞም፣“አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።

11. እንደ ገናም፣“አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል።

12. ኢሳይያስም እንዲሁ፣“በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣የእሴይ ሥር ይመጣል፤በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል።

13. በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።

የአሕዛብ አገልጋይ የሆነው ጳውሎስ

14. ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀት ሁሉ እንደ ተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኜ አለሁ።

15. እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና ዐሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጒዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣

16. በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።

17. ስለዚህ እግዚአብሔርን በማገልገሌ በክርስቶስ ኢየሱስ እመካለሁ።

18. በተናገርሁትና በአደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤

19. ይህም የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ።

20. ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር።

21. ይልቁንም፣“ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

22. በዚህም ምክንያት ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ።

ሮምን ለመጐብኘት የጳውሎስ ዕቅድ

23. አሁን ግን በእነዚህ አካባቢዎች የምሠራው ስለሌለ፣ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ እናንተን ለማየት እናፍቅም ስለ ነበር፣

24. ይህን ዕቅድ ወደ እስጳንያ በምሄድበት ጊዜ ልፈጽመው አስባለሁ። በማልፍበትም ጊዜ ልጐበኛችሁና ከእናንተ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ በጒዞዬ እንደም ትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

25. አሁን ግን በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ነኝ።

26. ምክንያቱም መቄዶንያና አካይያ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል የሚገኙትን ድኾች ለመርዳት ተነሣሥተዋልና።

27. ርዳታ ለማድረግ ወደዋል፤ በርግጥም ባለ ዕዳዎቻቸው ናቸው። አሕዛብ የአይሁድ መንፈሳዊ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ፣ ያገኙትን ምድራዊ በረከት ከአይሁድ ጋር ይካፈሉ ዘንድ የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው።

28. ስለዚህ ሥራውን ከጨረስሁና ይህን ፍሬ መቀበላቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ እግረ መንገዴንም እናንተን አያለሁ።

29. ወደ እናንተም ስመጣ፣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ ዐውቃለሁ።

30. ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የተጋድሎዬ አጋር እንድትሆኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ።

31. በይሁዳ ካሉት ከማያምኑት እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለው አገልግሎቴም በዚያ ባሉት ቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤

32. ይኸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተም ጋር እንድታደስ ነው።

33. የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።