ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አብርሃም በእምነት ጸደቀ

1. እንግዲህ በሥጋ የቀድሞ አባታችን የሆነ አብርሃም በዚህ ረገድ ምን አገኘ እንላለን?

2. አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ፣ የሚመካበት ነበረው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት መመካት አይችልም።

3. መጽሐፍስ ምን ይላል? “አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።”

4. አንድ ሰው ሥራ ከሠራ ደመወዙ እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ተገቢ ዋጋው ይቈጠርለታል።

5. ነገር ግን ለማይሠራው፣ ኃጥኡን ሰው ጻድቅ በሚያደርግ በእግዚአብሔር ለሚያምን ሰው፣ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል።

6. ዳዊትም ጽድቅ ያለ ሥራ ስለሚቈጠርለት ሰው ብፅዕና እንዲህ ብሎአል፤

7. “መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፣ኀጢአታቸው የተሰረየላቸው፣ብፁዓን ናቸው።

8. ኀጢአቱን፣ ጌታ ከቶ የማይቈጥርበት ሰውብፁዕ ነው።”

9. ይህ ብፅዕና ለተገረዙት ብቻ ነው ወይስ ላልተገረዙትም? የአብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት ብለናል።

10. ታዲያ እንዴት ተቈጠረለት? ከተገረዘ በኋላ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? የተቈጠረለት ከተገረዘ በኋላ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው።

11. ሳይገረዝ በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ፣ የመገረዝን ምልክት ይኸውም የጽድቅን ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ለሚያምኑ ነገር ግን ላልተገረዙት ጽድቅ ይቈጠርላቸው ዘንድ የሁሉ አባት ነው።

12. እርሱ ለተገረዙትም አባት ነው፤ መገረዝ ብቻ ሳይሆን፣ አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉ ነው።

13. እርሱ የዓለም ወራሽ እንዲሆን አብርሃምና ዘሩ ተስፋን የተቀበሉት በሕግ በኩል አልነበረም፤ ነገር ግን በእምነት ከሆነው ጽድቅ ነው።

14. በሕግ የሚኖሩት ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት የማይጠቅም፣ ተስፋም ከንቱ በሆነ ነበር፤

15. ሕግ ቊጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም።

16. ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቶአል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የእርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው፤

17. ይህም “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው።

18. “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለእርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ።

19. እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም።

20. ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤

21. እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር።

22. ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።”

23. “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለእርሱ ብቻ አይደለም፤

24. ነገር ግን እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ ለሚቈጥርልን፣ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው በእርሱ ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው።

25. እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።