ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእግዚአብሔር ታማኝነት

1. ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? መገረዝስ ምን ፋይዳ አለው?

2. በየትኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው ለእነርሱ ነው።

3. አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን?

4. ፈጽሞ አይሆንም! ሰው ሁሉ ሐሰተኛ፣ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ፣በፍርድም ፊት ረቺ ትሆናለህ።”

5. የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጒልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቊጣውን ማምጣቱ ትክክል አይደለም ሊባል ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው።

6. በርግጥ እንዲህ ሊሆን አይችልም፤ እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል?

7. “የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈርድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል።

8. ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው።

ማንም ጻድቅ አይደለም

9. እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋል፤

10. እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድም እንኳ፤

11. አስተዋይ የለም፤እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም።

12. ሁሉም ተሳስተዋል፤በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤በጎ የሚያደርግ ማንም የለም፤አንድም እንኳ።”

13. “ጒሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤አንደበታቸው ሽንገላን ያዘወትራል።”“በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።”

14. “አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።”

15. “እግራቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣን ነው፤

16. በመንገዳቸው ጥፋትና ጒስቊልና ይገኛል፤

17. የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”

18. “በዐይናቸው ፊት የእግዚአብሔር ፍርሀት የለም።”

19. እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ፣ እናውቃለን፤

20. ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም በእርሱ ፊት ጻድቅ ነው ሊባል አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን።

በእምነት የሚገኝ ጽድቅ

21. አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጦአል።

22. ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤

23. ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል፤

24. በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤

25. በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤

26. በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን፣ ለማሳየት ነው።

27. ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ።

28. ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን።

29. እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፤ የአሕዛብም አምላክ ነው፤

30. የተገረዘውን በእምነት፣ ያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና።

31. ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከእምነት የተነሣ ሕግን ዋጋ የሌለው እናደርግ ይሆን? ፈጽሞ አይደረግም፤ ሕጉን እናጸናለን እንጂ።