ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእስራኤል ትሩፋን

1. እንግዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተዋቸውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! እኔ ራሴ ከብንያም ነገድ፣ የአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ።

2. እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። ኤልያስ በእስራኤል ላይ ክስ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንዳቀረበ፣ መጽሐፍ ስለ እርሱ ምን እንደሚል አታውቁምን?

3. “ጌታ ሆይ፤ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ሊገድሉኝም ይፈልጋሉ።”

4. እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ግን ምን ነበር? “ለበኣል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ።”

5. በአሁኑ ጊዜም እንደዚሁ በጸጋ የተመረጡ ትሩፋን አሉ።

6. እንግዲህ በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም፤ በሥራ ቢሆንማ ኖሮ ጸጋ፣ ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።

7. እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ልባቸው ደነደነ፤

8. እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ዐይናቸው እንዳያይ፣ጆሮአቸውም እንዳይሰማ፣እግዚአብሔር እስከዚህ ቀን ድረስ፣የድንዛዜ መንፈስ ሰጣቸው።”

9. ዳዊትም አለ፤“ማእዳቸው አሽክላና ወጥመድ፣ዕንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው።

10. ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጋረዱ፤ወገባቸውም ለዘላለም ይጒበጥ።”

የተዳቀሉ ቅርንጫፎች

11. ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይደለም፤ ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቶአል።

12. ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸውምን ያህል ታላቅ በረከትያመጣ ይሆን?

13. አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤

14. ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው።

15. የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

16. በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።

17. ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣

18. በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ ግን አንተን ይሸከምሃል እንጂ።

19. እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል።

20. ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን።

21. እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና።

22. እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭካኔ ተመልከት፤ ጭካኔውም በወደቁት ላይ ነው፤ ቸርነቱ ግን በቸርነቱ ውስጥ እስካለህ ድረስ ለአንተ ነው፤ ያለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ።

23. እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ፣ ተመልሰው ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያስገባቸው ይችላልና።

24. የበረሓ ከሆነው የወይራ ዛፍ የተቈረጥህና ተፈጥሮህ ወዳልሆነው ወደ መልካሙ ወይራ የገባህ ከሆንህ፣ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት እነዚህ ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ መግባታቸውማ ምን ያህል ይሆን?

እስራኤል ሁሉ ይድናል

25. ወንድሞች ሆይ፤ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ፣ ይህን ምስጢር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ፣ እስራኤል በከፊል በድን ዳኔ ውስጥ ዐልፋለች።

26. ስለዚህ እስራኤል ሁሉ ይድናሉ፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል።

27. ኀጢአታቸውንም ሳስወግድ፣ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳኔ ይህ ነው።”

28. እንደ ምሥራቹ ቃል ለእናንተ ሲባል ጠላቶች ናቸው፤ እንደ ምርጫ ከሆነ ግን፣ ለአባቶች ሲባል የተወደዱ ናቸው፤

29. የእግዚአብሔር ስጦታና ጥሪ ጸጸት የለበትም።

30. እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ እንደ ነበራችሁ፣ ከእነርሱ አለመታዘዝ የተነሣ አሁን ምሕረት እንዳገኛችሁ ሁሉ፣

31. እግዚአብሔር ለእናንተ ምሕረት ከማድረጉ የተነሣ፣ እነርሱም ምሕረት ያገኙ ዘንድ አሁን የማይታዘዙ ልጆች ሆነዋል፤

32. እግዚአብሔር ለሁሉም ምሕረት ያደርግ ዘንድ ሰውን ሁሉ ባለመታዘዝ ዘግቶታልና።

ውዳሴ

33. የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው!ፍርዱ አይመረመርም፤ለመንገዱም ፈለግ የለው … 

34. “የጌታን ልብ ያወቀ ማነው?አማካሪውስ የነበረ ማን ነው?”

35. “እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው?”

36. ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።