ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ፣ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራና ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየ፤

2. ስለዚህ ወንጌል በነቢያቱ በኩል በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞተስፋ ተሰጠ።

3. ወንጌሉም ስለ ልጁ፣ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ሆነ፣

4. በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

5. በእርሱ በኩል ስለ ስሙ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል ሰዎችን በእምነት አማካይነት ወደሚገኘው መታዘዝ ለመጥራት ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን።

6. እናንተ ራሳችሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከተጠሩ መካከል ናችሁ።

7. በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ በሮም ላላችሁ ሁሉ፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ሮምን ለማየት የጳውሎስ ናፍቆት

8. ከሁሉ አስቀድሜ፣ እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁም አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።

9. ዘወትር ምን ያህል እንደማስባችሁ፣ የልጁን ወንጌል በመስበክ በሙሉ ልቤ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤

10. በጸሎቴ ሁል ጊዜ አስባችኋለሁ፤ አሁን ደግሞ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ እንድመጣ መንገድ ይከፈትልኝ ዘንድ እጸልያለሁ።

11. እንድትጸኑ የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ አካፍላችሁ ዘንድ፣ ላያችሁ እናፍቃለሁ።

12. ይኸውም እናንተና እኔ በእያንዳንዳችን እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።

13. ወንድሞች ሆይ፤ በሌሎች አሕዛብ ዘንድ እንደሆነልኝ፣ በእናንተም ዘንድ ፍሬ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ ዐቅጄ ሳለሁ፣ እስከ አሁን ድረስ ግን መከልከሌን እንድታውቁ እወዳለሁ።

14. ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ፣ ዕዳ አለብኝ፤

15. በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው።

16. በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ ይህም በመጀመሪያ ለአይሁድ፣ ቀጥሎም ለአሕዛብ ነው።

17. በወንጌል የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጦአልና፤ ጽድቁም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእምነት የሆነ ነው፣ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው።

የእግዚአብሔር ቊጣ በሰዎች ላይ

18. በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል፤

19. ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል።

20. ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም።

21. እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ።

22. ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤

23. የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረት መልክ መስለው ለወጡ።

24. ስለዚህም እግዚአብሔር በኀጢአት በተሞላው የልባቸው ምኞት እርስ በርሳቸው የገዛ አካላቸውን እንዲያስነውሩ ቅድስና ለሌለው ሩካቤ ሥጋ አሳልፎ ሰጣቸው።

25. የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፤ አገለገሉም፤ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው፤ አሜን።

26. በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አሳፋሪ ለሆነ ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም እንኳ ለባሕርያቸው የሚገባውን ግንኙነት ባሕርያቸው ላልሆነው ግንኙነት ለወጡ።

27. እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ ለክፉ አድራጐታቸውም የሚገባቸውን ቅጣት በገዛ ራሳቸው ላይ አመጡ።

28. ከዚህም በላይ በሐሳባቸው እግዘአብሔርን ማወቅ አይጠቅምም በማለታቸው፣ መደረግ የማይገባውን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው።

29. በሁሉም ዐይነት ዐመፃ፣ ክፋት፣ ስግብግብነትና ምግባረ ብልሹነት ተሞልተዋል፤ ቅናትን፣ ነፍስ ገዳይነትን፣ ጥልን፣ አታላይነትንና ተንኰልን የተሞሉ ናቸው፤ ሐሜተኞች፣

30. ስም አጥፊዎች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞችና ትምክሕተኞች ናቸው፤ ክፋትን የሚሠሩበትን መንገድ ያውጠነጥናሉ፤ ለወላጆቻቸው አይታዘዙም።

31. የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ርኅራኄ የሌላቸውና ጨካኞች ናቸው።

32. ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ።