ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የግል ሰላምታ

1. በክንክራኦስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነችውን እኅታችንን ፌቤንን ዐደራ እላችኋለሁ።

2. ለቅዱሳን ተገቢ በሆነው አቀባበል በጌታ እንድትቀበሏትና ከእናንተም የምትፈልገውን ማንኛውንም ርዳታ እንድታደርጉላት አሳስባችኋለሁ፤ ለብዙ ሰዎችና ለእኔም ጭምር ታላቅ ድጋፍ ነበረችና።

3. በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚያገለግሉት ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

4. እነርሱም ለእኔ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሰጡ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያመሰግኗቸዋል።

5. በእነርሱ ቤት ላለች ቤተ ክርስቲያንም ሰላምታ አቅርቡልኝ።ከእስያ አገር ለመጀመሪያ ወደ ክርስቶስ ለተመለሰው፣ ለወዳጄ ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

6. ለእናንተ ብዙ ለደከመችው ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

7. ከእኔ ጋር ታስረው ለነበሩት ዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱ በሐዋርያት መካከል ስመጥሮችና በክርስቶስ በማመንም እኔን የቀደሙ ናቸው።

8. በጌታ ለምወደው ለጵልያጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

9. በክርስቶስ አብሮን ለሚሠራው ለኢሩባኖንና ለውድ ወዳጄ ለስንጣክን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

10. በክርስቶስ ያለው እምነቱ ተፈትኖ ለተመሰገነው ለኤጤሌን ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ከአርስጣባሉ ቤተ ሰብ ለሆኑትም ሰላምታ አቅርቡልኝ።

11. ለዘመዴ ለሄሮድዮና ሰላምታ አቅርቡልኝ፤በጌታ ላሉት ለንርቀሱ ቤተ ሰቦች ሰላምታ አቅርቡልኝ።

12. በጌታ ሆነው በትጋት ለሚሠሩት ሴቶች፣ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ።በጌታ ሆና እጅግ ለደከመችው ለሌላዋ ሴት፣ ለተወደደችው ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

13. በጌታ ለተመረጠው ለሩፎንና የእኔም እናት ለሆነችው ለእናቱ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

14. ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ፣ ለሄሮሜን፣ ለጳጥሮባን፣ ለሄርማን፣ ከእነርሱም ጋር ላሉት ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ።

15. ለፍሌጎን፣ ለዩልያ፣ ለኔርያና ለእኅቱ፣ እንዲሁም ለአልንጦን፣ ከእነርሱም ጋር ላሉት ቅዱሳን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

16. በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

17. ወንድሞች ሆይ፤ መለያየትን ከሚፈጥሩትና የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም በጒዞአችሁ መሰናክል ከሚያደርጉት እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ።

18. እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን፣ የራሳቸውን ሆድ ነው፤ በለሰለሰ አንደ በታቸውና በሽንገላ፣ የዋሆችን ያታልላሉ።

19. የእናንተን ታዛዥነት ሁሉም ሰምተዋል፤ በዚህም እኔ እጅግ ተደስቻለሁ። ሆኖም በጎ ስለ ሆነው ነገር ጥበበኞች፣ ክፉ ስለ ሆነውም የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።

20. የሰላም አምላክ፣ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል።የጌታችን የኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

21. አብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ፣ እንዲሁም ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስ፣ ኢያሶንና ሱሲጴጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

22. ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ፣ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።

23. በመልካም መስተንግዶው እኔና በዚህ የምትገኘዋ መላዋ ቤተ ክርስቲያን ደስ የምንሰኝበት ጋይዮስ፣ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።የከተማዪቱ ግምጃ ቤት ሹም የሆነው ኤርስጦስ፣ ወንድማችንም ቊአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

24. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

25-26. በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ ሕዝቦች ሁሉ አምነው እንዲታዘዙ፣ በነቢያት መጻሕፍት አሁን በተገለጠው፣ ላለፉት ረጅም ዘመናት ተሰውሮ በነበረው ምስጢር መገለጥ መሠረት፣ በአስተማርሁት ወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ መሰበክ ሊያጸናችሁ ለሚችለው፣

27. እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።