ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሰለጰዓድ ሴት ልጆች

1. የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የአፌር ልጅ፣ የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ጐሣዎች ነበሩ፤ ስማቸውም ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካና ቲርጻ ይባላል። እነርሱም፣

2. ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ ቀረቡ፤ በሙሴ፣ በካህኑ በአልዓዛር፣ በመሪዎችና በመላው ማኅበርም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፤

3. “አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ ተባብረው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ካመፁት ከቆሬ ተከታዮች ጋር አልነበረም፤ የሞተው ግን በራሱ ኀጢአት ሲሆን፣ ወንዶች ልጆችም አልነበሩትም።

4. ታዲያ አባታችን ወንድ ልጅ ባለመውለዱ ስሙ ከጐሣዎቹ ተለይቶ እንዴት ይጠፋል? ለእኛም በአባታችን ዘመዶች መካከል ርስት ስጡን።”

5. ስለዚህ ሙሴ ጒዳያቸውን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረበ፤

6. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤

7. “የሰለጰዓድ ልጆች ጥያቄ ትክክል ነው፤ በእርግጥ በአባታቸው ዘመዶች መካከል ድርሻቸውን ርስት አድርገህ ልትሰጣቸው ስለሚገባ የአባታቸውን ድርሻ ለእነርሱ አስተላልፍላቸው።

8. “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይተካ ቢሞት ውርሱን ለሴት ልጁ አስተላልፉ።

9. ሴት ልጅ ከሌለችው ደግሞ ውርሱን ለወንድሞቹ ስጡ።

10. ወንድሞች ከሌሉትም ውርሱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ።

11. አባቱ ወንድሞች ከሌሉትውርሱ ከጐሣው መካከል ቅርብ ለሆነ ዘመዱ ይሰጥ፤ እርሱም ይውረሰው። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን ሕጋዊ መመሪያ ይሆናቸዋል።’ ”

ኢያሱ በሙሴ እግር ተተካ

12. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በዓባሪም ሸንተረር ላይ ወዳለው ወደዚህ ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የሰጠኋቸውን ምድር እይ።

13. ካየኸውም በኋላ አንተም እንደ ወንድምህ እንደ አሮን ወደ ሕዝብህ ትሰበሰባለህ፤

14. ምክንያቱም ማኅብረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው።

15. ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤

16. “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆነ ጌታ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ማኅበረሰብ ላይ ሰው ይሹም፤

17. እርሱም፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን በፊቱ የሚወጣና የሚገባ፣ መርቶ የሚያወጣውና የሚያገባው እንዲሆን ነው።”

18. ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት።

19. በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በፊታቸውም ሹመው፤

20. መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲታዘዝለትም ከሥልጣንህ ከፍለህ ስጠው።

21. እርሱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእርሱም ቃል ይገባሉ።”

22. ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው የእስራኤል ማኅበር ፊት አቆመው፤

23. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት እጁን በራሱ ላይ ጭኖ ሾመው።