ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከእግዚአብሔር የወረደ እሳት

1. በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ስለ ደረሰባቸው ችግር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አጒረመረሙ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ማጒረም ረማቸውን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነደደች፤ ከሰፈሩም ዳርቻ ጥቂቱን በላች።

2. ሕዝቡ ወደ ሙሴ ጮኸ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች።

3. ከዚህ የተነሣም የቦታው ስም፣ “ተቤራ” ተባለ፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እሳት በመካከላቸው ነዳለችና።

እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የላከላቸው ድርጭት

4. ድብልቁ ሕዝብ ሌላ ምግብ ጐመጀ፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ያጒረመርሙ ጀመር፤ “ምነው የምንበላው ሥጋ ባገኘን ኖሮ!

5. በግብፅ ያለ ምንም ዋጋ የበላ ነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል።

6. አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቶአል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!”

7. መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው።

8. ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር።

9. ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር።

10. ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ።

11. እርሱም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “እንዲህ ያለውን መከራ በባሪያህ ላይ ለምን አመጣህ? የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝስ ምን አስቀይሜህ ነው?

12. ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድ ነው?

13. ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል።

14. እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም።

15. እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”

16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋር ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ።

17. ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል።

18. “ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብፅ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰምቶአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ።

19. የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለአምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤

20. ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብፅ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ”

21. ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺህ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤

22. ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?”

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክንድ ይህን ያህል አጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት።

24. ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው።

25. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም።

26. ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ።

27. አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው።

28. ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ።

29. ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ተቈርቍረህ ነውን? የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤

30. ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ።

31. በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው፤

32. በዚያን ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግሥቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት።

33. ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ።

34. ሌላ ምግብ ለማግኘት የጐመጁትን ሰዎች በዚያ ስለ ቀበሩአቸው የቦታው ስም “ቂብሮት ሃታአባ” ተባለ።

35. ሕዝቡም ከቂብሮት ሃታአባ ወደ ሐጼሮት ተጒዘው እዚያው ሰፈሩ።