ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ተጨማሪ ቊርባን

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እንድትኖሩበት ወደምሰጣችሁ ምድር ከገባችሁ በኋላ፣

3. ስእለታችሁን ለመፈፀም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማድረግ ወይም በተወሰኑ በዓሎቻችሁ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ከላም ወይም ከበግ መንጋ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ስታቀርቡ

4. መሥዋዕቱን ይዞ የሚመጣው ሰው በኢን አንድ አራተኛ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት የእህል ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቀርባል።

5. ለሚቃጠል ወይም ለዕርድ መሥዋዕት ከሚቀርብ ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ የመጠጥ ቊርባን አብራችሁ አዘጋጁ።

6. “ ‘ከአውራ በግ ጋር በኢን ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ፤

7. እንዲሁም ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢን አንድ ሦስተኛ የወይን ጠጅ አዘጋጁ፤ ይህንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ሽታ ያለው አድርጋችሁ አቅርቡ።

8. “ ‘አንዱን ወይፈን ለተለየ ስለት ወይም ለኅብረት የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የዕርድ መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታዘጋጁበት ጊዜ፣

9. ከወይፈኑ ጋር በግማሽ ኢን ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት አብራችሁ አምጡ።

10. እንዲሁም ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን ግማሽ ኢን የወይን ጠጅ አቅርቡ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብና ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል።

11. እያንዳንዱ ወይፈን ወይም አውራ በግ፣ እያንዳንዱ የበግም ሆነ የፍየል ጠቦት በዚህ ሁኔታ ይዘጋጅ።

12. ባዘጋጃችሁት ቍጥር ልክ ይህን ለእያንዳንዱ አድርጉ።

13. ማናቸውም የአገር ተወላጅ የሆነ በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች በዚሁ ሁኔታ ያድርግ።

14. ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ መጻተኛ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማናቸውም ሰው በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ልክ እናንተ እንደምታደርጉት ያድርግ።

15. ማኅበረ ሰቡ ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ አንድ ዐይነት ደንብ ይኖረዋል፤ ይህም በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ የማይሻር ሥርዐት ነው። እናንተም ሆናችሁ መጻተኞቹ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እኩል ትታያላችሁ፤

16. ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ይኸው ሕግና ሥርዐት እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።’ ”

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

18. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እኔ ወደምወስዳችሁ ምድር ገብታችሁ፣

19. የምድሪቱን በረከት ስትመገቡ ከዚሁ ላይ አንሥታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊርባን አቅርቡ።

20. ይህንም ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ ኅብስት ጋግራችሁ ከዐውድማ እንደ ተገኘ ቊርባን አድርጋችሁ አምጡ።

21. በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ አንሥታችሁ ይህን ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትሰጣላችሁ።

ባለማወቅ ስለሚደረግ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት

22. “ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዛት አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት

23. እግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዛቱን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ትውልዶች በሙሴ አማካይነት ያዘዛችሁን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፣

24. ይህም የተፈጸመው ሆን ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋር ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቊርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ።

25. ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ፤ ምክንያቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለ ሆነና ስለ ስሕተታቸውም በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) ስላቀረቡ ነው።

26. ባለማወቅ የተደረገውን ስሕተት ሁሉም የፈጸሙት ስለ ሆነ፣ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብና በመካከላቸው የሚኖር መጻተኛ ሁሉ ይቅር ይባላል።

27. “ ‘ነገር ግን አንድ ሰው ካለማወቅ የተነሣ በግሉ ኀጢአት ቢሠራ ግን ለኀጢአት መሥዋዕት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያምጣ።

28. ከዚያም ካህኑ፣ ባለማወቅ ኀጢአት ሠርቶ ለተሣሣተው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስርየት በሚደረግለትም ጊዜ ሰውየው ይቅር ይባላል።

29. ያገር ተወላጅ እስራኤላዊ ይሁን ወይም መጻተኛ ባለማወቅ ኀጢአት ከሠራ በማናቸውም ሰው ላይ ሕጉ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

30. “ ‘ያገር ተወላጅም ይሁን መጻተኛ ሆን ብሎ ኀጢአት የሚሠራ ማንኛውም ሰው ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ስለሚያቃልል ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ።

31. የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ስለናቀ፣ ትእዛዛቱንም ስለ ጣሰ ያ ሰው በእርግጥ ተለይቶ መጥፋት አለበት፤ ጥፋቱ የራሱ ነው።’ ”

ሰንበትን የሻረው በሞት ተቀጣ

32. እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን ዕንጨት ሲለቅም ተገኘ።

33. ዕንጨት ሲለቅም ያገኙትም ሰዎች ሰውየውን ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበር አመጡት፤

34. በሰውየው ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ በጥበቃ ሥር እንዲቈይ አደረጉት።

35. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሰውየው ይሙት፤ መላውም ማኅበር ከሰፈር ውጭ በድንጋይ ይውገረው” አለው፤

36. ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ማኅበሩ ሰውየውን ከሰፈር አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው።

ስለ ልብስ ዘርፍ የተሰጠ መመሪያ

37. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

38. “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ በየልብሳችሁ ጫፍ ላይ ዘርፍ አድርጉ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው።

39. ልባችሁ የተመኘውን፣ ዐይናችሁ ያየውን ሁሉ ተከትላችሁ እንዳታመነዝሩ እነዚህን ዘርፎች በማየት የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዛት በማስታወስ እንድትታዘዙ ማስታወሻ ይሆኑአችኋል።

40. ስለዚህ ትእዛዛቴን ሁሉ ለመፈጸም ታስባላችሁ፤ ለአምላካችሁም (ኤሎሂም) የተቀደሳችሁ ትሆናላችሁ።

41. አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነኝ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።