ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቀዓታውያን

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2. “ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቊጠሩ።

3. እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠሩ።

4. “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅዱሳቱን መጠበቅ ነው።

5. ሰፈሩ ሲነሳ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤

6. ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ።

7. “በኅብስተ ገጹ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁል ጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ።

8. በእነዚህም ላይ ቀይ ጨርቅ ይዘርጉ፤ የአቆስጣውን ቍርበት ደርበውም መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

9. “ደግሞም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው ማብሪያ መቅረዙንና መብራቶቹን፣ መኮስተሪያዎቹንና የኵስታሪ መቀበያዎቹን፣ እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን የዘይት ዕቃዎች ይሸፍኑበት።

10. ከዚያም ይህንና ከዚሁ ጋር የተያያዙትን ዕቃዎች ሁሉ በአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

11. “በወርቅ መሠዊያ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ዘርግተው በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

12. “እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት።

13. “ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤

14. ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ።

15. “አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅዱሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅዱሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው።

16. “የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።”

17. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

18. “የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤

19. ወደ ንዋየ ቅዱሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት።

20. ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅዱሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳን ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”

ጌድሶናውያን

21. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

22. “ጌድሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቊጠራቸው፤

23. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቊጠር።

24. “የጌድሶናውያን የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤

25. እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤

26. እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ።

27. የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ።

28. እንግዲህ የጌድሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል።

ሜራሪያውያን

29. “ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቊጠራቸው፤

30. እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር።

31. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤

32. እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋር ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት።

33. እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።”

የሌዋውያን ጐሣዎች ቈጠራ

34. ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው።

35. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኖአቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣

36. በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ።

37. ይህ ከቀዓት ጐሣዎች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው። ሙሴና አሮን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ቈጠሯቸው።

38. ጌድሶናውያን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።

39. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ሃምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣

40. በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሣ ነበሩ።

41. ይህ ከጌድሶን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

42. ሜራሪያውያንም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር።

43. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣

44. በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።

45. ይህ የሜራሪ ጐሣዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው።

46. ስለዚህ ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች ሌዋውያኑን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው፤

47. ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኖአቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ለመስጠትና ለመሸከም የመጡት፣

48. ቍጥራቸው ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ።

49. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ በየአገልግሎቱና በየሸክም ሥራው ተደለደለ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ቈጠራቸው።