ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የካህናትና የሌዋውያን ተግባር

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “መቅደሱን በተመለከተ ስለሚፈጸም በደል አንተ፣ ልጆችህና የአባትህ ቤተ ሰቦች ኀላፊነቱን ትሸከማላችሁ፤ ክህነቱን በተመለከተ ስለሚፈጸም በደል ግን ኀላፊነቱ የሚወድቀው በአንተና በልጆችህ ላይ ብቻ ነው።

2. አንተና ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት በምታገለግሉበት ጊዜ አብረዋችሁ እንዲሆኑና እንዲረዱአችሁ ከአባትህ ነገድ ሌዋውያንን አምጣቸው።

3. እነርሱም በአንተ ኀላፊነት ሥር ሆነው የድንኳኑን አገልግሎት በሙሉ ያከናውኑ፤ ይሁን እንጂ ወደ መቅደሱ ዕቃዎችም ሆነ ወደ መሠዊያው አይጠጉ፤ ከተጠጉ ግን እነርሱም አንተም ትሞታላችሁ።

4. እነርሱም የመገናኛውን ድንኳን ለመንከባከብ ማለትም በድንኳኑ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ኀላፊነት በመውሰድ አብረዋችሁ ይሁኑ፤ ከዚህ በተረፈ ግን እናንተ ወዳላችሁበት ማንም ሰው አይጠጋ።

5. “በእስራኤላውያን ላይ ዳግም ቊጣ እንዳይደርስባቸው የመቅደሱና የመሠዊያው እንክብካቤ ኀላፊነት የሚመለከተው እናንተን ይሆናል።

6. ከእስራኤላውያን መካከል ወገኖቻችሁን ሌዋውያንን ለእናንተ ስጦታ አድርጌ እኔ ራሴ መርጫቸዋለሁ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ ሁሉ እንዲሠሩ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጡ ናቸው።

7. ይሁን እንጂ በመሠዊያው ላይ የሚደረገውንና በመጋረጃ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም የክህነት አገልግሎት የምትፈጽሙት አንተና ልጆችህ ብቻ ናችሁ፤ የክህነቱን አገልግሎት ስጦታ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከእናንተ በስተቀር ወደ መቅደሱ የሚጠጋ ቢኖር ግን ይገደል።”

ለካህናትና ለሌዋውያን የሚሰጡ መባዎች

8. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ለእኔ በሚቀርበው መባ ላይ ኀላፊነትን የሰጠሁህ እኔው ራሴ ነኝ፤ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝም የተቀደሰ መባ ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ መደበኛ ድርሻችሁ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ።

9. ለእኔ ከሚቀርብልኝ እጅግ ከተቀደሰው መባ ሁሉ፣ በእሳት የማይቃጠለው የራስህ ድርሻ ይሆናል፤ እጅግ የተቀደሰ አድርገው ከሚያመጡልኝ ስጦታ ከእህል ቊርባንም ሆነ ከኀጢአት ወይም ከበደል መሥዋዕት የሚነሣው ሁሉ የአንተና የልጆችህ ድርሻ ነው።

10. እጅግ ቅዱስ መሆኑን በማሰብ በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ እያንዳንዱም ወንድ ከዚሁ ይብላ፤ ይህ ለአንተም የተቀደሰ ነው።

11. “እስራኤላውያን ከሚያቀርቡት ስጦታ፣ ከሚወዘወዘው ቊርባን ተለይቶ የሚቀመጠው ስጦታ ሁሉ የአንተ ይሁን። ይህንም ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት የነጻ ማንኛውም ሰው ከዚሁ መብላት ይችላል።

12. “እስራኤላውያን የመከር በኵራት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጡትን ምርጥ የወይራ ዘይት በሙሉ፣ ምርጥ የሆነውን አዲስ የወይን ጠጅና እህል ሁሉ ለእናንተ ሰጥቻችኋለሁ።

13. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያመጡት የምድሪቱ በኵር ፍሬ ሁሉ የአንተ ይሆናል። ከቤተ ሰዎችህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይህን መብላት ይችላል።

14. “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ የተሰጠ በእስራኤል ያለ ማንኛውም ነገር ሁሉ የአንተ ነው።

15. ማሕፀን የሚከፍትና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ሰውም ሆነ እንሰሳ የአንተ ነው፤ ነገር ግን ማንኛውም በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅና ንጹሕ ካልሆነ እንስሳ በኵር ሆኖ የተወለደውን ተባዕት ሁሉ ዋጀው።

16. እነዚህም አንድ ወር ሲሆናቸው ሃያ ጌራ በሚመዝነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ፣ በተወሰነው በመዋጃው ዋጋ በአምስት ሰቅል ጥሬ ብር ትዋጀዋለህ።

17. “የተቀደሱ ስለሆኑ የበሬ፣ የበግ ወይም የፍየል በኵር የሆኑትን አትዋጃቸውም፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፤ ሥባቸውንም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ ታቃጥለዋለህ።

18. የሚወዘወዘው ቊርባን ፍርምባና የቀኙ ወርች የአንተ እንደሆነ ሁሉ የእነዚህም ሥጋ የአንተ ይሆናል።

19. እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያቀርቡት ከተቀደሰ ቊርባን የሚለየው ሁሉ ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለአንተና ለዘሮችህ ዘላለማዊ የጨው ኪዳን ነው።”

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፣ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም፤ በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።

21. “በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግሉበት ጊዜ ለሚሠሩት ሥራ ደመወዝ እንዲሆናቸው ከእስራኤል የሚወጣውን ዐሥራት ሁሉ ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ።

22. አድራጎቱ ኀጢአት ስለ ሆነ ሞት እንዳ ያስከትልባቸው ከእንግዲህ ወዲያ እስራኤላውያን ወደ መገናኛው ድንኳን አይጠጉ።

23. በመገናኛው ድንኳን የሚከናወነውን ሥራ የሚሠሩት ሌዋውያን ናቸው፤ በዚያም ለሚፈጸመው በደል ኀላፊነቱን ይሸከማሉ። ይህም ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው፤ ሌዋውያን በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይሰጣቸውም።

24. በዚህ ፈንታም እስራኤላውያን መባ አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን ዐሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም እነርሱን በተመለከተ፣ ‘በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይኖራቸውም’ ያልኩት በዚሁ ምክንያት ነው።”

25. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

26. “ሌዋውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጌ የምሰጣችሁን ዐሥራት ከእስራኤላውያን በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እናንተም ካገኛችሁት ላይ አንድ ዐሥርኛ በማውጣት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድጋችሁ ታቀርባላችሁ።

27. ቊርባናችሁም ከዐውድማ እንደ ገባ እህል ወይም ከመጭመቂያ እንደ ወጣ ወይን ሆኖ ይቈጠርላችኋል።

28. እናንተም ከእስራኤላውያን ላይ ከምትቀበሉት ዐሥራት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ ታቀርባላችሁ፤ ከዚሁም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የሆነውን ዐሥራት ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።

29. ከምትቀበሉት ሁሉ ምርጥና እጅግ የተቀደሰውን ክፍል የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ አድርጋችሁ ታቀር ባላችሁ።

30. “ሌዋውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ምርጥ የሆነውን ክፍል በምታቀርቡበት ጊዜ፣ እንደ ዐውድማ ምርት ወይም እንደ ወይን መጭመቂያ ውጤት ሆኖ ይቈጠርላችኋል።

31. የቀረው ግን በመገናኛው ድንኳን ለሰጣችሁት አገልግሎት ደመወዛችሁ ስለ ሆነ፣ እናንተና ቤተ ሰዎቻችሁ በየትኛውም ስፍራ ልትበሉት ትችላላችሁ።

32. የተመረጠውን ክፍል ካቀረባችሁ በዚህ በደለኞች አትሆኑም፤ ደግሞም የተቀደሰውን የእስራኤላውያንን መባ አታረክሱም፤ አትሞቱምም።