ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31
  32. 32
  33. 33
  34. 34
  35. 35
  36. 36

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘኁልቍ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሌዋውያን

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር፤

2. የአሮን ልጆች የበኵሩ ስም ናዳብ፣ የሌሎቹም አብዩድ አልዓዛርና ኢታምር ይባላል።

3. እርሱ ለክህነት አገልግሎት የለያቸው፣ ካህናት ለመሆን የተቀቡት የአሮን ወንድ ልጆች ስም ይህ ነው፤

4. ናዳብና አብዩድ ግን በሲና ምድረ በዳ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ እዚያው እፊቱ ወድቀው ሞቱ። ወንዶች ልጆች ስላልነበሯቸውም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን በክህነት ያገለግሉ ነበር።

5. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

6. “የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤

7. በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለእርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤

8. የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ።

9. ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለእርሱ ፈጽመው የተሰጡ ናቸው።

10. አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።”

11. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

12. “እነሆ፤ በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ወስጃለሁ፤ ስለዚህ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፤

13. በኵር የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና። በግብፅ ምድር በኵር የሆነውን ሁሉ በመታሁ ዕለት ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ማናቸውንም የእስራኤልን በኵር ለራሴ ለይቻለሁ፤ የእኔ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።”

14. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ፣

15. “ሌዋውያንን በየቤታቸውና በየጐሣቸው ቍጠር፤ የምትቈጥረውም አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ነው” አለው።

16. ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት እነዚህን ቈጠራቸው።

17. የሌዊ ልጆች ስምጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ነው።

18. የጌድሶን ልጆች ጐሣ ስምሎቢኒና ሰሜኢ ነው።

19. የቀዓት ጐሣዎች፤እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል።

20. የሜራሪ ጐሣዎች፤ሞሖሊና ሙሲ።እንግዲህ የሌዋውያን ጐሣዎች በየቤተ ሰባቸው ሲቈጠሩ እነዚህ ናቸው።

21. የሎቤናና የሰሜአ ጐሣዎች ከጌርሶን ወገን ናቸው፤ እነዚህ የጌርሶን ጐሣዎች ነበሩ።

22. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበር።

23. የጌርሶን ጐሣዎች በምዕራብ በኩል ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ይሰፍራሉ።

24. የጌርሶን ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።

25. የጌድሶናውያን ኀላፊነት በመገናኛው ድንኳን ማደሪያውንና ድንኳኑን፣ መደረቢያዎቹን እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያለውን መጋረጃ፣

26. የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ ማደሪያ ድንኳኑንና መሠዊያውን የሚጋርደውን የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹንና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ መጠበቅ ይሆናል።

27. የእንበረማውያን፣ የይሰዓራውያን፣ የኬብሮናውያንና የዑዝኤላውያን ጐሣዎች ከቀዓት ወገን ናቸው፤ እነዚህ የቀዓት ጐሣዎች ነበሩ።

28. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ሲሆን፣ ቀዓታውያንም መቅደሱን የመጠበቅ ኀላፊነት ነበራቸው።

29. የቀዓት ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።

30. የቀዓት ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል።

31. እነርሱም ታቦቱን፣ ጠረጴዛውን፣ መቅረዙን፣ መሠዊያዎቹን፣ ለመቅደሱ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች፣ መጋረጃዎችንና ከነዚህ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ይጠብቃሉ።

32. ዋናው የሌዋውያን አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው፤ እርሱም መቅደሱን ለመጠበቅ ኀላፊ በሆኑት ላይ ተሹሞ ነበር።

33. የሞሖላውያንና የሙሳያውያን ጐሣዎች ከሜራሪ ወገን ናቸው፤ እነዚህም የሜራሪ ጐሣዎች ነበሩ።

34. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች ሁሉ ብዛታቸው ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር።

35. የሜራሪም ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ይሆናል፤ የሜራሪም ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።

36. ሜራሪያውያንም የማደሪያውን ድንኳን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን እግሮች፣ የማደሪያ ዕቃዎችን ሁሉና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ለመጠበቅ ተሹመው ነበር።

37. እንዲሁም የአደባባዩን ዙሪያ ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ከነካስማቸውና ከነገመዶቻቸው ይጠብቃሉ።

38. ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ ከማደሪያው ድንኳን በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይሰፍራሉ፤ እነርሱም እስራኤላውያንን ወክለው ማደሪያ ድንኳኑን ለመጠበቅ ኀላፊዎች ይሆናሉ፤ ወደ ማደሪያው ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሌላ ሰው ግን ይገደል።

39. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው፣ ሙሴና አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየጐሣቸው የቈጠሩአቸው የሌዋውያን ወንዶች ልጆች ጠቅላላ ብዛት ሃያ ሁለት ሺህ ነበር።

40. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ።

41. በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።”

42. ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤

43. አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር።

44. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

45. “በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

46. ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣

47. ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለ ሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ልክ አምስት አምስት ሰቅል ተቀበል፤

48. የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።”

49. ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤

50. ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል ሰበሰበ።

51. ሙሴም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።