ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሆሴዕ 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኤፍሬም የነፋስ እረኛ ነው፤ቀኑን ሙሉ የምሥራቅን ነፋስ ይከተላል፤ሐሰትንና ዐመፅን ያበዛል።ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋል፤የወይራ ዘይትንም ወደ ግብፅ ይልካል።

2. እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የሚያቀርበው ክስ አለው፤ያዕቆብን እንደ መንገዱ ይቀጣዋል፤እንደ ሥራውም ይከፍለዋል።

3. በማሕፀን ሳለ የወንድሙን ተረከዝ ያዘ፤ሙሉ ሰውም ሲሆን ከአምላክ ጋር ታገለ።

4. ከመልአኩም ጋር ታገለ፤ አሸነፈውም፤በፊቱ ሞገስን ለማግኘት አልቅሶ ለመነው፣እርሱንም በቤቴል አገኘው፤በዚያም ከእርሱ ጋር ተነጋገረ፤

5. እርሱም ሁሉን የሚገዛ አምላክ እግዚአብሔር፣የሚታወቅበት ስሙም እግዚአብሔር ነው።

6. ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ፍቅርንና ፍትሕን ጠብቅ፤ዘወትርም በአምላክህ ታመን።

7. ነጋዴው በሐሰተኛ ሚዛን ይሸጣል፤ማጭበርበርንም ይወዳል።

8. ኤፍሬም እንዲህ እያለ ይታበያል፤“እኔ ባለጠጋ ነኝ፤ ሀብታምም ሆኛለሁ፤ይህ ሁሉ ሀብት እያለኝ፣ምንም ዐይነት በደል ወይም ኀጢአት አያገኙብኝም።”

9. “ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤በዓመት በዓላችሁ ቀን ታደርጉ እንደ ነበረው ሁሉ፣እንደ ገና በድንኳኖች እንድትቀመጡአደርጋችኋለሁ።

10. ለነቢያት ተናገርሁ፤ራእይንም አበዛሁላቸው፤በእነርሱም በኩል በምሳሌ ተናገርሁ።

11. ገለዓድ ክፉ ነው፤ሕዝቡም ከንቱ ናቸው፤ኮርማዎችን በጌልገላ ይሠዋሉን?መሠዊያዎቻቸው በታረሰ መሬት ላይ እንዳለ፣የድንጋይ ክምር ይሆናሉ።

12. ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሸሸ፤እስራኤል ሚስት ለማግኘት ሲል አገለገለ፤ዋጋዋንም ለመክፈል በጎችን ጠበቀ።

13. እግዚአብሔር በነቢይ አማካይነት እስራኤልን ከግብፅ አወጣ፤በነቢይም በኩል ተንከባከበው።

14. ኤፍሬም ግን ክፉኛ አስቈጣው፤ጌታውም የደም አፍሳሽነቱን በደል በላዩ ላይ ያደርግበታል፤ስለ ንቀቱም የሚገባውን ይከፍለዋል።