ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሆሴዕ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በእስራኤል ላይ የቀረበ ክስ

1. በምድሪቱ በምትኖሩ በእናንተ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ክስ ስላለው፣እናንት እስራኤላውያን ይህን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤“ታማኝነት የለም፤ ፍቅርም የለም፤እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድሪቱ የለም።

2. በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል።

3. ስለዚህ ምድሪቱ አለቀሰች፤በውስጧም የሚኖሩ ሁሉ ኰሰመኑ፤የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣የባሕርም ዓሦች አለቁ።

4. “ነገር ግን ማንም ሰው አይከራከር፤ማንም ሌላውን አይወንጅል፤በካህናት ላይ ክስን እንደሚያቀርቡ፣ሕዝብህ እንደዚያው ናቸውና።

5. ቀንና ሌሊት ትደናበራላችሁ፤ነቢያትም ከእናንተ ጋር ይደናበራሉ፤ስለዚህ እናታችሁን አጠፋታለሁ፤

6. ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል።“ዕውቀትን ስለናቃችሁ፣እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ።

7. ካህናት በበዙ ቊጥር፣በእኔ ላይ የሚያደርጉት ኀጢአት በዝቶአል፤ክብራቸውንም በውርደት ለውጠዋል።

8. የሕዝቤ ኀጢአት ለመብል ሆኖላቸዋል፤ርኵሰታቸውንም እጅግ ወደዱ።

9. ካህናትም ከሕዝቡ የተለዩ አይደሉም፤ሁሉንም እንደ መንገዳቸው እቀጣቸዋለሁ፤እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ።

10. “ይበላሉ ግን አይጠግቡም፤ያመነዝራሉ ግን አይበዙም፤ እግዚአብሔርን በመተው፣ራሳቸውን

11. ለአመንዝራነት፣ለአሮጌና ለአዲስ የወይን ጠጅ አሳልፈው ሰጡ፤በእነዚህም

12. የሕዝቤ ማስተዋል ተወሰደ፤ከዕንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቃሉ፤ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል።የአመንዝራነት መንፈስ ያስታቸዋል፤ለአምላካቸውም ታማኝ አልሆኑም።

13. በተራሮችም ጫፍ ላይ ይሠዋሉ፤መልካም ጥላ ባለው፣ በባሉጥ፣በኮምቦልና በአሆማ ዛፍ ሥር፣በኰረብቶችም ላይ የሚቃጠል ቊርባን ያቀርባሉ።ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማዊ፣ምራቶቻችሁም አመንዝራ ይሆናሉ።

14. “ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ሲሆኑ፣የልጆቻችሁም ሚስቶች ሲያመነዝሩአልቀጣቸውም።ወንዶች ከጋለሞቶች ጋር ይሴስናሉ፤ከቤተ ጣዖት ዘማውያን ጋር ይሠዋሉና፤የማያስተውል ሕዝብ ወደ ጥፋት ይሄዳል!

15. “እስራኤል ሆይ፤ አንቺ ብታመነዝሪም፣ይሁዳ በበደለኛነት አትጠየቅ።“ወደ ጌልገላ አትሂዱ፤ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፤‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁም አትማሉ።

16. እስራኤላውያን እንደ እልኸኛ ጊደር፣እልኸኞች ናቸው፤ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን በመልካም መስክ ውስጥ እንዳሉ የበግ ጠቦቶችእንዴት ያሰማራቸዋል?

17. ኤፍሬም ከጣዖት ጋር ተጣምሮአል፤እስቲ ተውት፤

18. መጠጣቸው ባለቀ ጊዜ እንኳ፣ዘማዊነታቸውን አያቆሙም፤ገዦቻቸውም ነውርን አጥብቀው ይወዳሉ።

19. ዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤መሥዋዕቶቻቸውም ኀፍረት ያመጡባቸዋል።