ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ

1. ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐፍሴባ ትባል ነበር።

2. ምናሴ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

3. አባቱ ሕዝቅያስ ያፈረሰውን የየኰረብታውን ማምለኪያ ስፍራ መልሶ ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም ለበኣል መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ ሠራ። እንዲሁም ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም።

4. እግዚአብሔር፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ።

5. በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ መሠዊያ ሠራ።

6. የገዛ ልጁን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ መተተኛና ጠንቋይ ሆነ፤ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ጠየቀ፤ እግዚአብሔርን ለቊጣ የሚያነሣሣውን ክፉ ድርጊት በፊቱ ፈጸመ።

7. የሠራውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ዐምድ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው።

8. እንዲሁም፤ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለ ዚሁ ስፍራ ነው።

9. ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው።

10. እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤

11. “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቶአል፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሞአል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቶአል።

12. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።

13. በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደ ሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።

14. የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ።

15. ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙና ለቊጣ ስላነሣሡኝ ነው።”

16. ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17. በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

18. ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሞን

19. አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች።

20. አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

21. አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም።

22. የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፤ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።

23. የአሞንም ሹማምት ዐመፁ፤ ንጉሡንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት።

24. ከዚያም የአገሩ ሕዝብ በንጉሥ አሞን ላይ ያመፁትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእግሩ ተክተው አነገሡት።

25. በአሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

26. እርሱም በዖዛ አትክልት ውስጥ ባለው መቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።