ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመበለቲቱ ዘይት

1. የነቢያት ማኅበር ወገን ከሆነው የአንደኛው ሚስት፣ “አገልጋይህ ባሌ ሞቶአል፤ እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበር አንተ ታውቃለህ፤ አሁን ግን ባለ ዕዳ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ባሪያ አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል” ስትል ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።

2. ኤልሳዕም፣ “ታዲያ እኔ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለ ንገሪኝ” አላት።እርሷም፣ “አገልጋይህ ከጥቂት ዘይት በቀር በቤቷ ምንም ነገር የላትም” አለች።

3. ኤልሳዕም እንዲህ አላት፤ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ፤

4. ገብተሽም መዝጊያውን ባንቺና በልጆችሽ ላይ የኋሊት ዝጊው፤ ዘይቱንም በማድጋዎቹ ሁሉ ጨምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ ሲሞላም ወደ አንድ በኩል አኑሪው።”

5. ስለዚህ ትታው ሄዳ መዝጊያውን በራሷና በልጆቿ ላይ የኋሊት ዘጋችው። ማድጎቹን እያቀረቡላትም እርሷ ትሞላ ጀመር።

6. ማድጋዎቹ ሁሉ ከሞሉ በኋላ ልጇን፣ “ሌላ ማድጋ አምጣ” አለችው።እርሱ ግን፣ “ምንም የቀረ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም ዘይቱ መውረዱን አቆመ።

7. እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።

የሱነማዪቱ ልጅ ከሞት ተነሣ

8. አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄደ። በዚያም አንዲት ሀብታም ሴት ነበረች፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር ምግብ ለመብላት ወደ ቤቷ ይገባ ነበር።

9. ሴቲቱም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ “ይህ አዘውትሮ በደጃችን የሚያልፍ ሰው፣ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ዐውቃለሁ፤

10. ስለዚህ በሰገነቱ ላይ አንዲት ትንሽ ክፍል ቤት ሠርተን ዐልጋና ጠረጴዛ፣ ወንበርና ፋኖስ እናስገባለን፤ ከዚያም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ማረፊያ ትሆነዋለች።”

11. አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያው መጥቶ ወደ ማረፊያ ክፍሉ በመውጣት ጋደም አለ።

12. አገልጋዩን ግያዝንም፣ “ሱነማዪቱን ጥራት” አለው፤ በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች።

13. ኤልሳዕም፣ “ ‘ለእኛ ስትይ በጣም ተቸግረሻል፣ ምን እንዲደረግልሽ ትፈልጊአለሽ? ለንጉሡ ወይስ ለሰራዊቱ አዛዥ የምንነግርልሽ ጒዳይ አለን?’ ብለህ ጠይቃት” አለው።ሴቲቱም መልሳ፣ “እኔ እኮ የምኖረው በገዛ ወገኖቼ መካከል ነው” አለችው።

14. ኤልሳዕም፣ “ታዲያ ምን ይደረግላት” ሲል ጠየቀ።ግያዝም፣ “ልጅ እኮ የላትም፤ ባሏም ሸምግሎአል” አለ።

15. ኤልሳዕም፣ “በል እንግዲያው ጥራት” አለው፤ እርሱም ጠርቶአት መጥታ እበራፉ ላይ ቆመች።

16. ኤልሳዕም የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ” አላት፤እርሷም፣ “አይደለም ጌታዬ፣ አንተ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ ኋላ አገልጋይህን መዋሸት እንዳይሆንብህ!” አለችው።

17. ሴትዮዋም ፀነሰች፤ ኤልሳዕ እንደ ነገራትም በተባለው ጊዜ ወንድ ልጅ ወለደች።

18. ሕፃኑ አደገ፤ አንድ ቀንም አባቱ ከዐጫጆች ጋር ወደነበረበት ቦታ ሄደ።

19. አባቱንም፣ “ራሴን! ራሴን!” አለው። አባቱም አገልጋዩን፣ “ተሸክመህ ወደ እናቱ አድር ሰው” አለው።

20. አገልጋዩም አንሥቶ እናቱ ዘንድ አደረሰው፤ ልጁም እስከ እኩለ ቀን ድረስ በእናቱ ጭን ላይ ተቀመጠ፤ ከዚያም ሞተ።

21. ወደ ላይ ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው ዐልጋ ላይ አስተኛችው፤ በሩንም ዘግታበት ወጣች።

22. ከዚያም ባሏን ጠርታ፣ “ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እንድመለስ አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ” አለችው።

23. ባሏም፣ “ዛሬ ወደ እርሱ መሄድ ለምን አስፈለገሽ? መባቻ ወይም ሰንበት አይደል” አላት።እርሷም፣ “ምንም አይደል፤ ልሂድ” አለችው።

24. ከዚያም አህያውን ጭና አገልጋይዋን፣ “ቶሎ ቶሎ ንዳ፤ እኔ ካልነገርኩህ በቀር ለእኔ ብለህ አታዝግም” አለችው።

25. ስለዚህ ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደች።የእግዚአብሔር ሰው በሩቁ ሲያያት አገልጋዩን ግያዝን እንዲህ አለው፤ “ሱነማዪቱን አየሃት፤ ያቻትና!

26. በል ሩጠህ ሂድና፣ ምነው ደኅና አይደለሽምን? ባልሽ ደኅና አይደለምን? ልጅሽስ ደህና አይደለምን? ብለህ ጠይቃት።”እርሷ፣ “ሁሉ ነገር ደህና ነው” አለች።

27. የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ተራራ ስትደርስም እግሩ ላይ ተጠመጠመች፤ ግያዝ ሊያስለቅቃት ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር ሰው ግን፣ “እጅግ አዝናለችና ተዋት! እግዚአብሔር ይህን ለምን ከእኔ እንደሰወረውና እንዳልነገረኝ አልገባኝም” አለ።

28. እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ለመሆኑ እኔ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‘አጒል ተስፋ እንዳትሰጠኝ’ አላልሁህምን?” አለችው።

29. ኤልሳዕም ግያዝን፣ “እንግዲህ ወገብህን ታጠቅ፤ በትሬን ያዝና ሩጥ፤ መንገድ ላይ ሰው ብታገኝ ሰላም አትበል፤ ማንም ሰው ሰላም ቢልህ መልስ አትስጥ፤ በትሬንም በልጁ ፊት ላይ አድርግ” አለው።

30. የልጁ እናት ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው፤ ስለዚህ ተነሥቶ ተከተላት።

31. ግያዝም ቀድሞአቸው ሄዶ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገ፤ ነገር ግን ድምፅም፣ ምላሽም አልነበረም። ስለዚህ ግያዝ ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ፣ “ልጁ አልነቃም” አለው።

32. ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባም ልጁ ሞቶ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።

33. ወደ ውስጥም ገባ፤ ከዚያም በሩን በራሱና በልጁ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

34. በዐልጋው ላይ ወጥቶም በልጁ ላይ ተጋደመና አፉን በአፉ፣ ዐይኑን በዐይኑ፣ እጁን በእጁ ላይ አደረገ። ሙሉ በሙሉ እንደተ ዘረጋበትም፣ የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ።

35. ኤልሳዕም ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ከሄደ በኋላ ወደ ዐልጋው ወጥቶ እንደ ገና በልጁ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተዘረጋበት፤ ልጁም ሰባት ጊዜ አስነጠሰውና ዐይኖቹን ከፈተ።

36. ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ፣ “ሱነማዪቱን ጥራት፤” አለው፤ እርሱም ጠራት። እንደ መጣችም፣ “በይ ልጅሽን ውሰጂ” አላት።

37. እርሷም ገብታ በእግሩ ላይ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጇንም ይዛ ወጣች።

መርዛሙ ወጥ

38. ኤልሳዕ ወደ ጌልገላ ተመለሰ፤ በዚያም አገር ራብ ነበረ። የነቢያት ማኅበር በፊቱ ተቀምጠው ሳለ አገልጋዩን፣ “ትልቁን ምንቸት ጣድና ለእነዚህ ሰዎች ወጥ ሥራላቸው” አለው።

39. ከእነርሱም አንዱ ቅጠላ ቅጠል ለማምጣት ወደ ሜዳ ወጥቶ፤ ዱር በቀል ሐረግ አገኘ፤ ከሐረጉም ላይ የቅል ፍሬ ለቅሞ በልብሱ ሙሉ ይዞ ተመለሰና ቈራርጦ በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደሆን ግን ማንም አላወቀም።

40. ሰዎቹ እንዲመገቡትም ወጡ ወጣ፤ ገና አንደ ቀመሱትም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ በምንቸቱ ውስጥ የሚገድል መርዝ አለ!” ብለው ጮኹ፤ ሊመገቡትም አልቻሉም።

41. ኤልሳዕም፣ “እስቲ ዱቄት አምጡልኝ” አለ። ያንንም በምንቸቱ ውስጥ ጨምሮ፣ “እንዲመገቡት ለሰዎቹ አቅርቡላቸው” አለ። በምንቸቱም ውስጥ ጒዳት የሚያስከትል ነገር አልተገኘም።

አንድ መቶ ሰው ተመገበ

42. አንድ ሰው ከበኵራቱ ፍሬ የተጋገረ ሃያ የገብስ ሙልሙልና ጥቂት የእሸት ዛላዎች በአቊማዳ ይዞ ከበኣልሻሊሻ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ። ኤልሳዕም አገልጋዩን፣ “ሰዎቹ እንዲበሉት ስጣቸው” አለው።

43. አገልጋዩም፣ “ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው አቀርባለሁ?” ሲል ጠየቀ፤ኤልሳዕ ግን፣ “እንዲበሉት ለሰዎቹ ስጣቸው፤ እግዚአብሔር፣ ‘በልተው ይተርፋቸዋል’ ይላልና” አለው።

44. ከዚያም አቀረበላቸው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረውም በልተው ተረፋቸው።