ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገ

1. እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር።

2. ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው፣ እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ ካንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ አብረው ወደ ቤቴል ወረዱ።

3. በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው አውቀሃልን?” አሉት።ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ።

4. ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።

5. በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት።እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ።

6. ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7. ከነቢያትም ማኅበር አምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ።

8. ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ።

9. ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድ ርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ።

10. ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ ያለበለዚያ ግን አይሆንም” አለው።

11. እያዘገሙም ሲነጋገሩ ሳለ፣ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረሶች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ።

12. ኤልሳዕም ይህን አይቶ፣ “አባቴ አባቴ የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች!” ብሎ ጮኸ፤ ዳግመኛም ኤልያስን አላየውም፤ ከዚያም የገዛ ልብሱን ይዞ ከሁለት ቦታ ቀደደ።

13. እርሱም ከኤልያስ የወደቀውን ካባ አነሣ፤ ተመልሶም በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ቆመ።

14. ከኤልያስ፣ የወደቀውንም ካባ ይዞ ውሃውን መታና፣ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ። ውሃውን ሲመታውም በግራና በቀኝ ተከፍሎለት ተሻገረ።

15. ከኢያሪኮም መጥተው ይህን ያዩ የነበሩት የነቢያት ወገኖች፣ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል” አሉ፤ ሊያገኙትም ሄደው በፊቱ ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡ።

16. ከዚያም፣ “እነሆ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ አምሳ ጠንካራ ሰዎች አሉን፤ ምናልባትም የእግዚአብሔር መንፈስ ጌታህን አንሥቶ ከአንዱ ተራራ ላይ አስቀምጦት ወይም ከአንዱ ሸለቆ አግብቶት ይሆናልና እስቲ ሄደው ይፈልጉት” አሉት። ኤልሳዕም፣ “አይሆንም፤ አትላኳቸው” አለ።

17. አይሆንም ለማለት ዕፍረት እስኪሰማው ድረስ ግድ አሉት፤ ስለዚህ፣ “በሉ እንግዲያው ላኳቸው” አለ። እነርሱም አምሳ ሰዎች ላኩ፤ ሰዎቹም ሦስት ቀን ሙሉ ፈልገው ሳያገኙት ቀሩ።

18. በኢያሪኮ ቈይቶ ወደ ነበረው ወደ ኤልሳዕ በተመለሱም ጊዜ፣ “ቀድሞውንስ ቢሆን አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።

የውሃው መፈወስ

19. የከተማዪቱም ሰዎች ኤልሳዕን፣ “እነሆ ጌታችን፤ እንደምታያት ይህች ከተማ ለኑሮ የተመቸች ናት፤ ይሁን እንጂ ውሃው መጥፎ ሲሆን ምድሪቱም ፍሬ የማትሰጥ ናት” አሉት።

20. እርሱም፣ “እስቲ በአዲስ ማሰሮ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ” አለ፤ እንዳለውም አመጡለት።

21. ከዚያም ወደ ውሃው ምንጭ ሄዶ ጨው ጣለበትና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ውሃ ፈውሸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ለሞት ምክንያት አይሆንም፤ ምድሪቱንም ፍሬ እንዳትሰጥ አያደርጋትም’ አለ።”

22. ኤልሳዕ እንደ ተናገረውም ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ የተፈወሰ ነው።

በኤልሳዕ ላይ አፌዙበት

23. ኤልሳዕም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድ ላይ ሲሄድ ሳለም ልጆች ከከተማ ወጥተው፣ “አንተ መላጣ፤ ውጣ!አንተ መላጣ ውጣ!” እያሉ አፌዙበት።

24. ኤልሳዕም ዘወር ብሎ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ ከዚያም ሁለት እንስት ድቦች ከዱር ወጥተው ከልጆቹ አርባ ሁለቱን ሰባበሯቸው።

25. እርሱም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።