ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጎቶልያና ኢዮአስ

1. የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን በሰማች ጊዜ፣ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች።

2. የንጉሥ ኢዮራም ልጅ፣ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት ግን የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሊገደሉ ከነበሩት ልዑላን መካከል ሰርቃ ወሰደችው። እንዳይገድሉትም ከጎቶልያ በመደበቅ እርሱንና ሞግዚቱን በአንድ እልፍኝ ሸሸገቻቸው።

3. ጎቶልያ አገሩን በምትገዛበት ጊዜም ከሞግዚቱ ጋር ስድስት ዓመት በእግዚአብሔር ቤት ተሸሸገ።

4. በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው።

5. እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤

6. ሌላው ከሦስት አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ።

7. እናንተ እንደተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን ቤተ መቅደስ ጠብቁ።

8. ሁላችሁም መሣሪያችሁን ይዛችሁ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ቢኖር ግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ አትለዩት።”

9. የመቶ አለቆቹም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።

10. ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሥ ዳዊትን ጦርና ጋሻ ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።

11. ወታደሮቹም እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን ይዘው፣ ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።

12. ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጠው፣ መንገሡን ዐወጀ፤ ኢዮአስም ተቀብቶ ነገሠ። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።

13. ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደች።

14. እነሆ፤ በወጒ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀዳ፣ “ይህ ክዳት ነው! ክዳት ነው!” በማለት ጮኸች።

15. ካህኑ ዮዳሄም ጭፍሮቹን የሚያዙትን የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤ የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ በሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤት መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር።

16. ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት ስፍራ ስትደርስ፣ ይዘው እዚያው ገደሏት።

17. ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ።

18. የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ሄደው አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ።

19. ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ ካራውያንንና ዘበኞቹን እንዲሁም የአገሩን ሕዝብ በሙሉ በመያዝ ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ንጉሡን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወስደው በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ታች ወዳለው ቤተ መንግሥት ይዘውት ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤

20. የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አለው፤ ጎቶልያ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሰይፍ ተገድላ ስለ ነበር፣ ከተማዪቱ ጸጥ አለች።

21. ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።