ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሕጉ መጽሐፍ ተገኘ

1. ኢዮስያስ ሲነግሥ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የባሱሮት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች።

2. ኢዮስያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ።

3. በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤

4. “ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤

5. ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤

6. የሚከፍሉትም ለአናጺዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት።

7. ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።”

8. ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው።

9. ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ሄዶ ለንጉሡ፣ “ሹማምትህ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተዋል፤ ቤተ መቅደሱን እየተቈጣጠሩ ለሚያሠሩትም አስረክበዋል” አለው።

10. ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት።

11. ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።

12. ከዚያም ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓክቦርን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤

13. “ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ምን እንደሆነ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የሚነደው የእግዚአብሔር ቊጣ ታላቅ ነውና።”

14. ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም የምትኖረው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ሰፈር ነበር።

15. ነቢዪቱም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤

16. “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ አመጣለሁ።

17. እኔን ስለተውኝና ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው በሠሯቸውም አማልክት ሁሉ ስላስቈጡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፣ አይጠፋምም።’ ”

18. እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ይህን ንገሩት፣ ‘ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤

19. “ለርግማንና ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን ስትሰማ ልብህ ስለ ተነካና ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀደህ በፊቴ ስላለቀስህ እግዚአብሔር ሰምቼሃለሁ ብሏል።

20. ስለዚህ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ ወደ መቃብር በሰላም ትወርዳለህ፤ በዚህ ቦታም የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሱን ለንጉሡ ይዘውለት ሄዱ።