ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በምንዝር የተያዘች ሴት

1. ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።

2. በማለዳም በቤተ መቅደስ አደባባይ እንደ ገና ታየ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ሊያስተምራቸውም ተቀመጠ።

3. የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በምንዝር የተያዘች ሴት አመጡ፤ በሕዝቡም ፊት አቁመዋት፣

4. ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤

5. ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዞናል፤ አንተስ ምን ትላለህ?”

6. ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው።ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ጀመር።

7. በጥያቄ ሲወተውቱት ቀና ብሎ፣ “ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” አላቸው።

8. እንደ ገናም ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ።

9. ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ።

10. ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት።

11. እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች።ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።

የኢየሱስ ምስክርነት እውነት መሆኑ

12. ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።

13. ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምት መሰክር፣ ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት።

14. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም።

15. እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤

16. ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው።

17. የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፎአል።

18. ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።”

19. ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት።ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።

20. ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።

21. ኢየሱስም እንደ ገና፣ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት ግን ልትመጡ አትችሉም” አላቸው።

22. አይሁድም፣ “ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ ያለው ራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ።

23. እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።

24. በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና።”

25. እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እስካሁን የነገርኋችሁ እኔ እርሱ ነኝ፤

26. በእናንተ ላይ ብዙ የምናገረውና ብዙ የምፈርደው ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ ታማኝ ነው፤ ከእርሱም የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ።”

27. እነርሱም ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አላስተዋሉም።

28. ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤

29. የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”

30. ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

የአብርሃም ልጆች

31. ኢየሱስም በእርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤

32. እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”

33. እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።

34. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤

35. ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምንጊዜም በቤት ይኖራል።

36. እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ።

37. የአብርሃም ልጆች መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል።

38. እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”

39. እነርሱም፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” ብለው መለሱለት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር።

40. ከእግዚአብሔር ሰምቼ እውነቱን የነገርኋችሁን እኔን ለመግደል ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል፤ አብርሃም ግን እንዲህ አላደረገም።

41. እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ የሚያደርገውን ነው።”እነርሱም፣ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ መለሱለት።

የዲያብሎስ ልጆች

42. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም።

43. የምናገረውን ለምን አታስተውሉም? ምክንያቱም ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው።

44. እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው፤

45. እኔ ግን እውነት ስለምናገር አታምኑኝም።

46. ከእናንተ ስለ ኀጢአት በማስረጃ ሊከሰኝ የሚችል አለን? እውነት የምናገር ከሆነ፣ ለምን አታምኑኝም?

47. ከእግዚአብሔር የሆነ እግዚአብሔር የሚለውን ይሰማል፤ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”

ኢየሱስ ስለ ራሱ የተናገረው

48. አይሁድም መልሰው፣ “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል ማለታችን ትክክል አይደለምን?” አሉት።

49. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔስ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ ጋኔን አላደረብኝም፤ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ።

50. እኔ የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ ግን አለ፤ ፈራጁም እርሱ ነው።

51. እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ቃሌን ቢጠብቅ፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም።”

52. አይሁድም እንዲህ አሉት፤ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን ዐወቅን፤ አብርሃም ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ማንም ቃልህን ቢጠብቅ ሞትን ፈጽሞ እንደማይቀምስ ትናገራለህ።

53. አንተ ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? እርሱ ሞተ፤ ነቢያቱም እንዲሁ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”

54. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ ግን እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።

55. እናንተ ባታውቁትም እኔ ዐውቀዋለሁ፤ አላውቀውም ብል፣ እኔም እንደ እናንተው ሐሰተኛ እሆናለሁ። እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ።

56. አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሤትም አደረገ።”

57. አይሁድም፣ “ገና አምሳ ዓመት ያልሞላህ፣ አንተ አብርሃምን አይተሃል!” አሉት።

58. ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” አላቸው።

59. በዚህን ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸው፤ ከቤተ መቅደስም ወጥቶ ሄደ።