ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ በተቃዋሚዎቹ መያዙ

1. ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ።

2. ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር።

3. ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር።

4. ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው።

5. እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር።

6. ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።

7. እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።

8. ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ፣ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤

9. ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።

10. ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ይባል ነበር።

11. ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው።

ኢየሱስ በሊቀ ካህናቱ በሐና ፊት ቀረበ

12. ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ ሎሌዎች ጋር በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣

13. በመጀመሪያ፣ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር።

14. ቀያፋም፣ ‘ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል’ ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር።

የጴጥሮስ ክህደት

15. ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤

16. ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ።

17. በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው።እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ።

18. ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።

ኢየሱስ በሊቀ ካህናቱ ፊት መቅረቡ

19. በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።

20. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም።

21. ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።”

22. ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው።

23. ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው።

24. ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።

የጴጥሮስ ሁለተኛና ሦስተኛ ክህደት

25. ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት።እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል ካደ።

26. ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከእርሱ ጋር አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው።

27. ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት

28. አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም።

29. ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው።

30. እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት።

31. ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት።

32. ይህ የሆነው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።

33. ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።

34. ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት።

35. ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው።

36. ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው።

37. ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው።ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው።

38. ጲላጦስም፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለው፤ ይህን ከተናገረ በኋላም እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ የሚያስከስስ በደል አላገኘሁበትም፤

39. ነገር ግን በፋሲካ አንድ እስረኛ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ ስለዚህ፣ ‘የአይሁድን ንጉሥ’ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?”

40. እነርሱም እንደ ገና በመጮኽ፣ “የለም፤ እርሱን አይደለም! በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።