ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ በቢታንያ ሽቱ መቀባቱ

1. የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ።

2. በዚያም ለኢየሱስ ሲባል ራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከእርሱ ጋር በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር።

3. ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በጠጒሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዓዛ ሞላው።

4. ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤

5. “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?”

6. ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቊሮ አልነበረም።

7. ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለ ሆነ እንድታቈየው ተዋት፤

8. ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁል ጊዜ አታገኙኝም።”

9. በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር።

10. ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤

11. ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።

ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ

12. በማግሥቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤

13. የዘንባባም ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤“ሆሣዕና!”“በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው!”“የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!”

14. ኢየሱስም የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

15. “የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገልተቀምጦ ይመጣል።”

16. ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለእርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር።

17. አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ ነበር።

18. ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ።

19. ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።

ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

20. ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ።

21. እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት።

22. ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት።

23. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሶአል፤

24. እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።

25. ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።

26. የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።

27. “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚች ሰዓት ታድነኝ? የለም፤ ይሁን የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና።

28. አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው።”ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።

29. በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ።

30. ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤

31. ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል።

32. እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።”

33. ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር።

34. ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።

35. ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።

36. የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም።

አይሁድ ባለማመን መጽናታቸው

37. ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤

38. ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣“ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ?የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።

39. ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤

40. “ዐይናቸውን አሳውሮአል፤ልባቸውንም አደንድኖአል፤ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤በልባቸውም አያስተውሉም፤እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።”

41. ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ።

42. ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር።

43. ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው።

44. ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤

45. እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።

46. በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።

47. “ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና።

48. በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም

49. እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ።

50. የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”