ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ከሞት ተነሣ

1. በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ፣ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄደች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ መግቢያ ተንከባሎ አየች።

2. ስለዚህም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ፣ “ጌታን ከመቃብር አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።

3. “ከዚያም ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ።

4. ሁለቱም ይሮጡ ነበር፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ጴጥሮስን ቀድሞት ከመቃብሩ ደረሰ።

5. ጐንበስ ብሎ ሲመለከት ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን በዚያው እንዳለ አየ፤ ወደ መቃብሩ ግን አልገባም።

6. ይከተለው የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ገባ፤ እርሱም ከተልባ እግር የተሠራውን ከፈን አየ፤

7. እንዲሁም በኢየሱስ ራስ ላይ ተጠምጥሞ የነበረውን ጨርቅ አየ፤ ይህም ጨርቅ ከከፈኑ ተለይቶ እንደ ተጠቀለለ ነበር።

8. ከዚያም አስቀድሞ ከመቃብሩ የደረሰው ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባ፤ አይቶም አመነ፤

9. ይኸውም ኢየሱስ ከሙታን መነሣት እንዳለበት ገና ከመጽሐፍ ስላልተረዱ ነበር።

ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ

10. ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ወደ የቤታቸው ሄዱ፤

11. ማርያም ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ታለቅስ ነበር፤ እያለቀሰችም መቃብሩን ለማየት ጐንበስ አለች።

12. የኢየሱስ ሥጋ በነበረበት ቦታ፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ ሌላው በግርጌ ተቀምጠው አየች።

13. እነርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት።እርሷም፣ “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አላውቅም” አለች።

14. ይህን ብላ ዘወር ስትል ኢየሱስ በዚያው ቆሞ አየች፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም።

15. እርሱም፣ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት።እርሷም የአትክልቱ ቦታ ጠባቂ መስሎአት፣ “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው።

16. ኢየሱስም፣ “ማርያም” አላት።እርሷም፣ ወደ እርሱ ዘወር ብላ በአራማይክ ቋንቋ፣ “ረቡኒ” አለችው፤ ትርጒሙም “መምህር ሆይ” ማለት ነው።

17. ኢየሱስም፣ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ፤ ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፣ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ’ ብሎአል ብለሽ ንገሪአቸው” አላት።

18. መግደላዊት ማርያምም፣ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ “ጌታን እኮ አየሁት!” አለች፤ እርሱ ያላትንም ነገረቻቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

19. በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

20. ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።

21. ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው።

22. ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤

23. የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

24. በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም።

25. ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት።እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ።

26. ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

27. ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው።

28. ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው።

29. ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው።

30. ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤

31. ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።