ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ

1. ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

2. በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ባለ መጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች።

3. በእነዚህም መመላለሻዎች ውስጥ ብዙ አካለ ስንኩላን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶችና ሽባዎች ይተኙ ነበር። [የውሃውንም መንቀሳቀስ እየተጠባበቁ፣

4. ዐልፎ ዐልፎ የጌታ መልአክ ወርዶ ውሃውን በሚያናውጥበት ጊዜ፣ ቀድሞ ወደ መጠመቂያዪቱ የገባ ካደረበት ማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።]

5. በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበር።

6. ኢየሱስም ይህን ሰው ተኝቶ ባገኘው ጊዜ፣ ለብዙ ጊዜ በዚህ ሁኔታ እንደ ነበር ዐውቆ “ልትድን ትፈልጋለህን?” አለው።

7. ሕመምተኛውም መልሶ፣ “ጌታዬ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መጠመቂያዪቱ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ይቀድመኛል” አለው።

8. ኢየሱስም፣ “ተነሥ! መተኛህን ተሸክመህ ሂድ” አለው።

9. ሰውየውም ወዲያው ተፈወሰ፤ መተኛውንም ተሸክሞ ሄደ።ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር።

10. አይሁድም የተፈወሰውን ሰው፣ “ሰንበት ስለ ሆነ መተኛህን እንድትሸከም ሕጉ አይፈቅድልህም” አሉት።

11. እርሱ ግን፣ “ያ የፈወሰኝ ሰው፣ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ብሎኛል” ሲል መለሰላቸው።

12. እነርሱም፣ “ ‘መተኛህን ተሸክመህ ሂድ’ ያለህ እርሱ ማነው?” ብለው ጠየቁት።

13. ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ወደ ሕዝብ መካከል ገብቶ ስለ ነበር፣ ሰውየው ማን እንደፈወ ሰው አላወቀም።

14. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶ፣ “እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥራ፤ ያለዚያ ከዚህ የባሰ ይደርስብሃል” አለው።

15. ሰውየውም የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው።

ወልድ ሕይወትን ይሰጣል

16. አይሁድም፣ በሰንበት ቀን እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸሙ፣ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር።

17. ኢየሱስም፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው።

18. እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።

19. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤

20. አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነ ቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል።

21. ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።

22. አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤

23. ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።

24. “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።

25. እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።

26. አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤

27. ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል።

28. “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤

29. መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።

30. እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው።

ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ ምስክርነቶች

31. “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ ተቀባይነት አይኖረውም።

32. ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደሆነ ዐውቃለሁ።

33. “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል፤

34. እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው።

35. ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሰኙ ወደዳችሁ።

36. “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል።

37. የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤

38. የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም።

39. በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤

40. እናንተ ግን፣ ሕይወት እንዲኖራችሁ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም።

41. “እኔ ከሰው ክብር አልቀበልም፤

42. ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ።

43. እኔ በአባቴ ስም መጥቼ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ።

44. እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትሰጣጡ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትፈልጉ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?

45. “ከሳሻችሁ ተስፋ የጣላችሁበት ሙሴ እንጂ፣ እኔ በአብ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤

46. ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ የጻፈው ስለ እኔ ነው።

47. እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ፣ እኔ የምናገረውን እንዴት ታምናላችሁ?”