ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊት የሳኦልን ሞት ሰማ

1. ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ በመመለስ፣ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቈየ።

2. በሦስተኛውም ቀን የተቀደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም፣ ወደ መሬት ለጥ ብሎ በአክብሮት እጅ ነሣ።

3. ዳዊትም፣ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር ሸሽቼ መምጣቴ ነው” በማለት መለሰለት።

4. ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ።

5. ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው።

6. ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤

7. ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም፣ ‘ምን ልታዘዝ’ አልሁ።

8. “እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፤“እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት።

9. “ከዚያም፣ ‘እኔ በሞት ጣር ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ።

10. “መቼም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፣ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፤ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።”

11. ከዚያም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።

12. ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፣ ለእግዚአብሔር ሰራዊትና ለእስራኤል ቤት አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ፤ የወደቁት በሰይፍ ነበርና።

13. ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም፣ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ።

14. ዳዊትም፣ “ታዲያ እግዚአብሔር የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው።

15. ዳዊትም ከጒልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “በል ቅረብና ውደቅበት” አለው። እርሱም መታው፤ ሞተም።

16. ዳዊትም፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፣ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።

ዳዊት ለሳኦልና ለዮናታን የተቀኘው የሐዘን እንጒርጒሮ

17. ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የሐዘን እንጒርጒሮ እየተቀኘ አለቀሰ፤

18. እንዲሁም የቀስት እንጒርጒሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።

19. “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቶአል፤ኀያላኑ እንዴት እንደዚህ ይውደቁ!

20. “ይህን በጌት አትናገሩ፤በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁት፤የፍልስጥኤም ቈነጃጅት አይደሰቱ፤ያልተገረዙት ሴቶች ልጆች እልል አይበሉ።

21. “እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤ጠል አያረስርሳችሁ፤ዝናብም አይውረድባችሁ፤የቍርባን እህል የሚያበቅሉም ዕርሻዎች አይኑራቸው፤በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፤ የሳኦል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም።

22. ከሞቱት ሰዎች ደም፣ከኀያላኑም ሥብ፣የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም።

23. “ሳኦልና ዮናታን በሕይወት እያሉ፣የሚዋደዱና የሚስማሙ ነበሩ፤ሲሞቱም አልተለያዩም፤ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች፣ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።

24. “እናንት የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፤ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፣ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፣ለሳኦል አልቅሱለት።

25. “ኀያላን እንዴት እንዲህ በጦርነት ወደቁ!ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቶአል።

26. ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤ከሴት ፍቅርም ይልቅ ግሩም ነበር።

27. “ኀያላኑ እንዴት ወደቁ!የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ከንቱ ይሁኑ!”