ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊትና ቤርሳቤህ

1. ነገሥታት ለጦርነት በሚወጡበት፣ በጸደይ ወራት ዳዊት ኢዮአብን ከንጉሡ ሰዎችና ከመላው የእስራኤል ሰራዊት ጋር አዘመተው፤ እነርሱም አሞናውያንን አጠፉ፤ ረባት የተባለችውንም ከተማ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።

2. አንድ ቀን ማታ፣ ዳዊት ከዐልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፣ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች።

3. ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ አጠያየቀ። ሰውየውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ።

4. ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች።

5. ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፣ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት።

6. ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት ላከው።

7. ኦርዮን በመጣ ጊዜም፣ ዳዊት የኢዮአብንና የሰራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው።

8. ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፣ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም ማለፊያ ምግብ አስከትሎ ላከለት።

9. ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ሁሉ ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ፣ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር።

10. ዳዊት፣ “ኦርዮን ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮን፣ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

11. ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፣ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ” አለው።

12. ከዚያም ዳዊት፣ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮን በዚያ ዕለትና በማግስቱ እዚያው ኢየሩሳሌም ቈየ።

13. በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮን በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አሽከሮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።

14. ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፤

15. በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ።

16. ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፣ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮን መደበው።

17. የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሰራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።

18. ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ።

19. መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣

20. ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል?

21. የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው።”

22. ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው።

23. መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው።

24. ከዚያም ባለ ፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፣ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።”

25. ዳዊትም፣ መልእክተኛውን፣ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን” ’ አለው።

26. የኦርዮን ሚስት ባሏ መሞቱን በሰማች ጊዜ አዘነች፤ አለቀሰችለትም።

27. የሐዘኑ ጊዜ ካበቃ በኋላም፣ ዳዊት ልኮ ቤርሳቤህን ወደ ቤቱ አስመጣት፤ ሚስቱ ሆነች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት የሠራው ሥራ እግዚአብሔርን አላስደሰተውም ነበር።