ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው።

2. ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ።

3. በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ።

4. ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ።

5. ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍ ረሃቸዋል።

6. የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ።

7. በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።”

8. ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የቤታቸው ሸሽተው ነበር።

ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ

9. በመላው የእስራኤል ነገዶችም፣ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዶአል፤

10. በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቶአል፤ ታዲያ ንጉሡን የመመለሱን ጒዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?”

11. ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለ ሆነ፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?

12. እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’

13. አሜሳ ይንም፣ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሰራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፣ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።”

14. እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም ሰዎችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት።

15. ከዚያም ንጉሡ ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ።በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር።

16. የብራቂም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ወረደ።

17. ከእርሱም ጋር አንድ ሺህ ብንያማውያን፣ እንዲሁም የሳኦል ቤተ ሰብ አገልጋይ ሲባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ በጥድፊያ ወረዱ።

18. የንጉሡን ቤተ ሰው ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ በመልካው ተሻገሩ።የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፣

19. እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አይቍጠርብኝ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከኢየሩሳሌም በወጣህባት ዕለት የፈጸምሁትን ስሕተት እርሳው፤ ከአእምሮህም አውጣው።

20. እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።”

21. ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለ ሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ።

22. ዳዊትም፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ።

23. ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

24. የሳኦል ልጅ ሜምፊቦስቴም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር።

25. እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

26. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ።

27. በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የባሪያህን ስም አጥፍቶአል፤ መቼም ንጉሥ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንህ ደስ ያለህን ሁሉ አድርግ።

28. የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን ባሪያህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”

29. ንጉሡም፣ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ ዕርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው።

30. ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።

31. እንዲሁም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ።

32. በዚያን ጊዜ ቤርዜሊ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በመሃናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር።

33. ንጉሡም ቤርዜሊን፣ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ እኔ እመግብሃለሁ” አለው።

34. ቤርዜሊ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው?

35. እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ ደግና ክፉውን መለየት እችላለሁ? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል?

36. አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው?

37. በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።”

38. ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው።

39. ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ከዚያ በኋላም ንጉሡ ተሻገረ። ንጉሡ ቤርዜሊን ስሞ መረቀው፤ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

40. ንጉሡ ወደ ጌልጌላ ሲሄድ፣ ከመዓም አብሮት ሄደ። የይሁዳ ሰራዊት በሙሉ እንዲሁም ግማሹ የእስራኤል ሰራዊት ንጉሡን አጅበው አሻገሩት።

41. ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው፣ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን በሹልክታ ለብቻቸው ይዘው እርሱንና ቤተ ሰውን ከተከታዮቹ ጋር ዮርዳኖስን ለምን አሻገሩ?” አሉት።

42. የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፣ ለእስራኤል ሰዎች፣ “ይህን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለ ሆነ ነው፤ ታዲያ ይህ እናንተን የሚያስቈጣ ነው? እኛ ከንጉሡ ተቀብለን አንዳች በልተናልን? ለራሳችንስ ምን የወሰድነው ነገር አለ?” አሉአቸው።

43. ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፣ “እኛ እኮ ከንጉሡ ዐሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ከዚህም በተጨማሪ በዳዊት ላይ ከእናንተ ይልቅ እኛ የበለጠ መብት አለን፤ ታዲያ እኛን የናቃችሁን ስለምንድን ነው? ንጉሣችን እንዲመለስ በመጀመሪያ የጠየቅ ነው እኛ አይደለንምን?” አሉ።ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር።