ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ።

2. ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤የበኵር ልጁ፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣

3. ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣ ሦስተኛው፣ ተልማይ ከተባለው ከጌሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣

4. አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣

5. ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው።

አበኔር ከዳዊት ጋር ተባበረ

6. የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ላይ ኀይሉን ያጠናክር ነበር።

7. ሳኦልም የኢዮሄልን ልጅ ሪጽፋን በቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው።

8. አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለተቈጣ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ የምወግን የውሻ ጭንቅላት ነኝን? ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ ታማኝነቴን እስከ ዛሬ ድረስ አላጓደልሁም፤ አንተንም አሳልፌ ለዳዊት አልሰጠሁም፤ አሁን ግን አንተ ከዚህች ሴት ጋር በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን?

9. እግዚአብሔር ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ እዳር እንዲደርስ ሳላደርግ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግበት፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤

10. የማለለትም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አውጥቶ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት የሰጠው ተስፋ ነው።”

11. ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም።

12. ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ተስማማ፤ እነሆ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ አንዲመለስ እኔ እረዳሃለሁ” ብለው ለዳዊት እንዲነግሩለት መልክተኞች ላከ።

13. ዳዊትም፣ “ይሁን እሺ፣ ከአንተ ጋር ስምምነቱን አደርጋለሁ፣ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ ያለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ።

14. ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት።

15. ስለዚህም ኢያቡስቴ መልክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፈልጢኤል ወሰዳት።

16. ባሏም እስከ ብራቂም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “በል በቃል! ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው። ስለዚህም ተመለሰ።

17. አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤

18. እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።”

19. እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።

20. አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው።

21. ከዚያም አበኔር ዳዊትን፤ “ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፣ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ሄጄ፣ ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።

ኢዮአብ አበኔርን ገደለው

22. የዳዊትና የኢዮአብ ሰዎች በዚያኑ ጊዜ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለሄደ፣ በኬብሮን አልነበረም።

23. ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መምጣቱን፣ ንጉሡ እንዳሰናበተውና እርሱም በሰላም እንደሄደ፣ ኢዮአብ ሰማ።

24. ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ እንዴት በሰላም እንዲሄድ አሰናበትኸው?

25. የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፣ መውጣት መግባትህን ለማወቅና የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልል ነው።”

26. ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ ወጣ፤ አበኔርን እንዲያመጡትም መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሴይር የውሃ ጒድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር።

27. አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፣ ኢዮአብ በቈይታ የሚያነጋግረው በመምሰል ዞር አድርጎ ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሲል፣ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው።

28. ዳዊት ይህን ነገር ቈይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤

29. ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቈዳ በሽታ ያለበት፣ በምርኵዝ የሚሄድ አንካሳ፣ ወይም በሰይፍ ተመቶ የሚወድቅ ወይም የሚበላው ያጣራብተኛ ከኢዮአብ ቤት አይታጣ።”

30. አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፣ እነርሱም አበኔርን ገደሉት።

31. ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቀዳችሁ፣ ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ራሱ ንጉሥ ዳዊትም አስከሬኑን አጀበ።

32. ከዚያም አበኔርን በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ጮኾ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ።

33. ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጒርጒሮ ተቀኘ፤“አበኔር እንደ ተራ ሰው ይሙት?

34. እጆችህ አልታሰሩም፤እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅአንተም እንደዚሁ ወደቅህ።”ሕዝቡም ሁሉ እንደ ገና አለቀሱለት።

35. ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እህል በሚቀምስበት ሰዓት ወደ ዳዊት መጥተው ምግብ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፣ “ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ።

36. ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመለከቱ፤ ደስም አላቸው፤ በእርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው።

37. እንዲሁም በዚያን ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልገባበት ዐወቁ።

38. ከዚያም ንጉሡ ለራሱ ሰዎች እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን?

39. ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፣ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።”