ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሳሙኤል መወለድ

1. በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ የኤያሬምኤል ልጅ፣ የኢሊዩ ልጅ፣ የቶሑ ልጅ፣ የናሲብ ልጅ፣ ነበረ።

2. እርሱም አንዲቱ ሐና፣ ሌላዪቱ ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍናና ልጆች ሲኖሯት፣ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።

3. ያም ሰው ሁሉን ቻይ ለሆነው ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የእግዚአብሔር ካህናት ነበሩ።

4. ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር።

5. ሐናን ግን ይወዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር።

6. እግዚአብሔር ማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር።

7. ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር።

8. ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።

9. አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።

10. ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች።

11. እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።”

12. ሐና ባለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።

13. እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምጿ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት።

14. እርሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት።

15. ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም።

16. ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭን ቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለ ሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቊጠረኝ።”

17. ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት።

18. እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።

19. በማግስቱ ጠዋት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤

20. ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል አለችው።

ሐና ሳሙኤልን ለእግዚአብሔር ሰጠች

21. ሰውየውም ሕልቃና ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ።

22. ሐና ግን አልሄደችም፤ እርሷም ባሏን፣ “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄ በእግዚአብሔር ፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” አለችው።

23. ባሏ ሕልቃናም፣ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥዪው ድረስ እዚሁ ቆዪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሐና ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች።

24. ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፣ በሴሎ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፣ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ።

25. ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት።

26. ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር ስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ።

27. ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ።

28. ስለዚህ እኔም ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገደ።