ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሩት 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቦዔዝ ሩትን አገባ

1. ቦዔዝም ወደ ከተማዪቱ በር አደባባይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ እርሱም የመቤዠት ቅድሚያ ያለው የቅርብ ዘመድ በመጣ ጊዜ፣ “ወዳጄ ሆይ፤ ወደዚህ ና፣ አጠገቤም ተቀመጥ” አለው፤ ስለዚህም ሰውየው ሄዶ ተቀመጠ።

2. ቦዔዝ ከከተማዪቱ ሽማግሌዎች ዐሥሩን ጠርቶ፣ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው፤ እነርሱም ተቀመጡ።

3. ከዚያም የመቤዠት ቅድሚያ ያለውን ቅርብ የሥጋ ዘመድ እንዲህ አለው፤ “ከሞዓብ የተመለሰችው ኑኃሚን፣ የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ መሬት ልትሸጥ ነው።

4. አንተም ይህንኑ ጒዳይ ማወቅ አለብህ ብዬ ስላሰብሁ፣ አሁን እዚህ በተቀመጡትና በሕዝቤም ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው ላሳስብህ ወደድሁ፤ አሁንም ራስህ የምትቤዠው ከሆነ ልትቤዠው ትችላለህ፤ ለዚህ ከአንተ ቅድሚያ የሚኖረው የለም፤ ይህን የማታደርግ ከሆነ ግን ከአንተ ቀጥሎ የሚገባኝ ስለ ሆንሁ፣ ንገረኝና ልወቀው።” ሰውየውም “እኔ እቤዠዋለሁ” አለ።

5. ከዚያም ቦዔዝ፣ “እንግዲህ መሬቱን ከኑኃሚንና ከሞዓባዊቷ ከሩት ላይ በምትገዛበት ዕለት የሟቹን ስም በርስቱ ለማስጠራት ሚስቱንም አብረህ መውሰድ አለብህ” አለው።

6. ያም ቅርብ የሥጋ ዘመድ፣ “እንዲህ ከሆነማ የራሴን ርስት አደጋ ላይ ልጥል ስለምችል፣ እኔ ልቤዠው አልችልም፤ አንተው ራስህ ተቤዠው” አለው።

7. በጥንት ዘመን በእስራኤል የመቤዠትም ሆነ ንብረት የማስተላለፍ ጒዳይ የሚጸናው አንዱ ወገን ጫማውን አውልቆ ለሌላው ወገን ሲሰጠው ነው፤ በእስራኤል ዘንድ መሸጥም ሆነ መግዛት ሕጋዊነት የሚኖረው በዚህ ሁኔታ ነበር።

8. ቅድሚያ ያለው ቅርብ የሥጋ ዘመድም ቦዔዝን፣ “እንግዲህ አንተው ራስህ ግዛው” ብሎ ጫማውን አወለቀ።

9. ቦዔዝም ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የአቤሜሌክን፣ የኬሌዎንንና የመሐሎንን ንብረት በሙሉ ከኑኃሚን ላይ ለመግዛቴ፣ በዛሬው ዕለት እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤

10. እንዲሁም የሟቹ ስም ከወንድሞቹ መካከልና ከአገሩ ደጅ እንዳይጠፋ፣ የሟቹን ስም በርስቱ ላይ ለማስጠራት የመሐሎን ሚስት የነበረችው ሞዓባዊት ሩትን አግብቼአታለሁ፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።”

11. ከዚያም ሽማግሌዎቹና በከተማዪቱ በር አደባባይ የነበሩት ሁሉ እንዲህ አሉ፤ “እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት፣ የእስራኤልን ቤት በአንድነት እንደሠሩ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ የበረታህ ሁን፤ ስምህም በቤተልሔም የተጠራ ይሁን።

12. እግዚአብሔር ከዚህች ወጣት ሴት በሚሰጥህ ዘር አማካይነት፣ ቤተ ሰብህን ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤተ ሰብ ያድርገው።”

የዳዊት የትውልድ ሐረግ

13. ስለዚህ ቦዔዝ ሩትን ወሰዳት፤ ሚስቱም ሆነች። ከዚያም ወደ እርሷ ገባ፤ እግዚአብሔር እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች።

14. ሴቶቹም ኑኃሚንን እንዲህ አሏት፤ “ዛሬ የሚቤዥ ቅርብ የሥጋ ዘመድ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ በመላው እስራኤልም ስሙ ይግነን።

15. ልጁ ሕይወትሽን ያድሳታል፤ በእርጅና ዘመንሽም ይጦርሻል፤ የምትወድሽና ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ ወልዳዋለችና።”

16. ከዚያም ኑኃሚን ሕፃኑን ተቀብላ ታቀፈችው፤ ሞግዚትም ሆነችው።

17. ጎረቤቶቿ የሆኑ ሴቶችም፣ “ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት” አሉ። ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት፤ እርሱም የዳዊት አባት የሆነው የእሴይ አባት ነበር።

18. እንግዲህ የፋሬስ ቤተ ሰብ ትውልድ ይህ ነው፦ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፤

19. ኤስሮምም አራምን ወለደ፤አራምም አሚናዳብን ወለደ፤

20. አሚናዳብም ነኦሶንን ወለደ፤ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤

21. ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፤ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፤

22. ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤እሴይም ዳዊትን ወለደ።