ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር።

2. ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ መጌዶን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤

3. ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም።

4. ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ።

5. አንዱ ዐለት በስተ ሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጊብዓ አንጻር ይገኝ ነበር።

6. ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና፤ ወደነዚያ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው።

7. ወጣቱም ጋሻ ጃግሬ፣ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው።

8. ዮናታንም እንዲህ አለው፣ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው።

9. እነርሱም፣ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፣ ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም።

10. ነገር ግን፣ ‘ወደ እኛ ውጡ’ ካሉን፣ እግዚአብሔር እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለ ሆነ፣ ወደ እነርሱ እንወጣለን።”

11. ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ በታዩ ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን፣ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጒድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ።

12. የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፣ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገር እናሳያችሁ” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው።ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፣ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና” አለው።

13. ዮናታን በእጁና በእግሩ ተፍጨርጭሮ፣ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተ ኋላው እየተከተለ ገደላቸው።

14. ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳይ አንድ ጥማድ በምታውል የዕርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ።

የፍስጥኤማውያን መሸነፍ

15. በሰፈር በዕርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር።

16. በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ዘቦች፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ።

17. ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፣ “እስኪ፣ ሰራዊቱን ቊጠሩና ማን ከዚህ እንደሄደ እዩ” አላቸው። ይህን ባደረጉ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።

18. ሳኦልም አኪያን፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ ታቦቱ በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።

19. ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፣ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፣ “እጅህን መልስ” አለው።

20. ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እነርሱም ፍልስጥኤማውያን በሰይፋቸው እየተጨፋጨፉ በታላቅ ትርምስ ላይ ሆነው አገኟቸው።

21. እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ገቡ።

22. በኰረብታማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፣ አጥብቀው በመከታተል አሳደዷቸው።

23. በዚያ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤት አዌን ዘልቆ ሄደ።

ዮናታን ማር በላ

24. ሳኦል፣ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለ ነበር፣ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።

25. ሰራዊቱ ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፣ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር።

26. ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፣ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሓላውን ፈርቶ ስለ ነበር፣ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም።

27. ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ።

28. ከዚያም አንዱ ወታደር፣ “አባትህ ሰራዊቱን፣ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት በጽኑ መሓላ አስሮአል። ሰው ሁሉ የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው” አለው።

29. ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሮአል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ።

30. ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቊጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”

31. በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ እጅግ ዝለው ነበር።

32. በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፣ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት።

33. ከዚያም ለሳኦል፣ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው።ሳኦልም፣ “ሕግ ተላልፋችኋል፤ በሉ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አቅርቡልኝ” አለ።

34. እርሱም፣ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፣ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ።ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ዐረደው።

35. ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።

36. ሳኦልም፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስ ቀርላቸው” አለ።እነርሱም፣ “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት።ካህኑ ግን፣ “እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አለ።

37. በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያች ቀን አልመለሰለትም።

38. ስለዚህ ሳኦል እንዲህ አለ፤ “የሰራዊቱ መሪዎች ሁላችሁም ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ምን ኀጢአት እንደ ተሠራ እንወቅ።

39. እስራኤልን የታደገ ሕያው እግዚአብሔርን! አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።

40. ሳኦልም እስራኤላውያንን ሁሉ፣ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው።ሰዎቹም፣ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ብለው መለሱለት።

41. ከዚያ በኋላ ሳኦል፣ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ” ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ።

42. ሳኦልም በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ።

43. ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፣ “እስቲ ያደረግኸውን ንገረኝ” አለው።ዮናታንም፣ “በዘንጌ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆ፤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።

44. ሳኦልም፣ “ዮናታን፣ አንተ ካልተገደልህ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፣ የከፋም ነገር ያምጣብኝ” አለ።

45. ሕዝቡ ግን ሳኦልን፣ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? አይደረግም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጠጒሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።

46. ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ እነርሱም ወደ አገራቸው ተመለሱ።

47. ሳኦል በእስራኤል ላይ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ፣ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ማለትም ሞዓብን፣ አሞናውያንን፣ ኤዶምን፣ የሱባን ነገሥታትና ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በሄደበት ሁሉ ድል ይነሣ ነበር።

48. በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው።

የሳኦል ቤተ ሰብ

49. የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ የሱዊ፣ሜልኪሳ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፣ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር።

50. የሳኦል ሚስት አኪናሆም የምትባል የአኪማአስ ልጅ ነበረች፤ የሰራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የአጎቱ የኔር ልጅ ነበረ።

51. የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር ሁለቱም የአቢኤል ልጆች ነበሩ።

52. በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ስለዚህ ሳኦል ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቊጥር ወደ ራሱ ወስዶ እንዲያገለግለው ያደርግ ነበር።