ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29
  30. 30
  31. 31

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የታቦቱ ወደ እስራኤል መመለስ

1. የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን ግዛት ሰባት ወር ቈየ።

2. ፍልስጥኤማውያን ካህናትንና ጠንቋዮችን ጠርተው፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ምን እናድርገው? ወደ ስፍራው እንዴት መመለስ እንደሚገባን ንገሩን” አሏቸው።

3. እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋር ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያ ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው።

4. ፍልስጥኤማውያንም፣ “የምንልከው የበደል መሥዋዕት ምን መሆን አለበት?” ሲሉ ጠየቁ።እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተንም ሆነ አለቆቻችሁን የመታው መቅሠፍት አንድ ዐይነት በመሆኑ፣ በፍልስጥኤማውያን ገዦች ቊጥር ልክ አምስት የወርቅ ዕባጮችና አምስት የወርቅ ዐይጦች ላኩ።

5. አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዐይነት ምስሎችን ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፣ ከአማልክታችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል።

6. እንደ ግብፃውያንና እንደ ፈርዖን ልባችሁን የምታደነድኑት ለምንድን ነው? እነርሱም እስራኤላውያንን የለቀቋቸው እግዚአብሔር በጽኑ ከቀጣቸው በኋላ አይደለምን?

7. “ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተ ጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞች አዘጋጁ። ላሞቹን በሠረገላው ጥመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ወደ ቤት መልሷቸው።

8. የእግዚአብሔርን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ በታቦቱም አጠገብ ባለው ሣጥን ውስጥ ለበደል መሥዋዕት የምትልኩትን የወርቅ ምስሎች አስቀምጡ፤ በፈለገውም መንገድ እንዲሄድ ልቀቁት፤

9. ነገር ግን ወዴት እንደሚሄድ ተመልከቱ፤ ወደ ቤትሳሚስ አቅጣጫ ወደ ገዛ አገሩ የሚሄድ ከሆነ፣ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው። ወደዚያ ካልሄደ ግን፣ መከራው በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የእርሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን።”

10. እነርሱም እንደዚሁ አደረጉ። ሁለቱን ላሞች ወስደው በሠረገላው ጠመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውንም በቤት ውስጥ ዘጉባቸው።

11. የእግዚአብሔርንም ታቦት፣ የወርቁን ዐይጦችና የዕባጮቹን ምስሎች በሠረገላው ላይ ጫኑ።

12. ከዚያም ላሞቹ መንገዳቸውን ይዘው እምቧ እምቧ እያሉ ቀጥ ብለው ወደ ቤትሳሚስ አመሩ። የፍልስጥኤም ገዦችም እስከ ቤትሳሚስ ድንበር ተከተሏቸው።

13. በዚህ ጊዜ የቤትሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴአቸውን ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው ሲመለከቱም ታቦቱን በማየታቸው በጣም ደስ አላቸው።

14. ሠረገላውም ወደ ቤትሳሚስ ወደ ኢያሱ ዕርሻ መጥቶ በአንድ ትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን ዕንጨት ፈልጠው፣ ሁለቱን ላሞች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር አቀረቡ።

15. ሌዋውያኑም የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የወርቅ ዕቃዎቹን ከያዘው ሣጥን ጋር አውርደው በትልቁ ድንጋይ ላይ አኖሩ። በዚያችም ዕለት የቤትሳሚስ ሕዝብ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ።

16. አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦችም ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ በዚያኑ ዕለት ወደ አቃሮን ተመለሱ።

17. ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የላኳቸው የወርቅ ዕባጮች አንዱ ስለ አሽዶድ፣ አንዱ ስለ ጋዛ፣ አንዱ ስለ አስቀሎና፣ አንዱ ስለ ጌትና አንዱ ስለ አቃሮን የቀረቡ ናቸው፤

18. የወርቅ ዐይጦቹም ቊጥር፣ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች በሚያስተዳድሯቸው የተመሸጉ ከተሞችና ከእነዚህ ውጭ ባሉት መንደሮቻቸው ቊጥር ልክ ነው። በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ ዕርሻ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታቦት ያስቀመጡበት ያ ትልቅ ድንጋይ እስከ ዛሬ ምስክር ነው።

19. ነገር ግን እግዚአብሔር ከቤትሳሚስ ሰዎች ጥቂቱን መታ፤ ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና ከመካከላቸው ሰባ ሰዎችን ገደለ፤ እግዚአብሔር እጅግ ስለ መታቸውም ሕዝቡ አለቀሰ።

20. የቤትሳሚስም ሰዎች፣ “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ማን መቆም ይችላል? ታቦቱስ ከዚህ ወጥቶ ወደ ማን ይሂድ?” አሉ።

21. ከዚያም ወደ ቂርያትይዓሪም ሰዎች መልእክተኞች ልከው፣ “ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰውልናል፤ ውረዱና ይዛችሁ ወደ ሰፈራችሁ ውጡ” አሏቸው።