ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ

1. ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል።

2. ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም።

3. እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።

4. እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።

5. መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፤

6. ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።

7. ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል።

8. ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።

9. ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ።

10. አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን?

11. ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው።

12. በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ።

13. ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።