ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሐዋርያ መብት

1. እኔ ነጻ ሰው አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ የድካሜ ፍሬዎች አይደላችሁምን?

2. ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ግን በርግጥ ሐዋርያ ነኝ፤ ምክንያቱም በጌታ የሐዋርያነቴ ማኅተም እናንተ ናችሁ።

3. ለሚመረምሩኝ የምሰጠው መልስ ይህ ነው።

4. ለመሆኑ፣ የመብላትና የመጠጣት መብት የለንምን?

5. እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ እንደ ጌታ ወንድሞችና እንደ ኬፋ ሁሉ፣ እኛስ አማኝ ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንምን?

6. ወይስ ጥረን ግረን መኖር ያለብን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?

7. ለመሆኑ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋ እየጠበቀ የከብቱን ወተት የማይጠጣ ማን ነው?

8. ይህን የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነውን? የኦሪትስ ሕግ ይህንኑ ይል የለምን?

9. በሙሴ ሕግ፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፎአልና። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔርን ያሳሰበው የበሬ ጒዳይ ነውን?

10. ይህን የተናገረው በርግጥ ስለ እኛ አይደለምን? የተጻፈው በትክክል ስለ እኛ ነው፤ ዐራሹ የሚያርሰው፣ አበራዩ የሚያበራየው ከምርቱ ድርሻ እንዳለው ተስፋ በማድረግ ነውና።

11. እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ዘር ዘርተን ከሆነ ለሥጋ የሚሆን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን?

12. ሌሎች ይህን መብት ከእናንተ ማግኘት ከቻሉ፣ እኛ ይበልጥ ማግኘት አይገባንምን?እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይልቁንም ለክርስቶስ ወንጌል ዕንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሣለን።

13. በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን?

14. እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዞአል።

15. እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና።

16. ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ።

17. በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል።

18. ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው።

19. እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ።

20. አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ።

21. እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ።

22. ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ።

23. ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።

24. በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ።

25. ለውድ ድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን።

26. ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ደግሞም ነፋስን እንደሚጐስም ሰው እንዲያው አልታገልም፤

27. ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።