ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በእስራኤል የደረሰው እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ

1. ወንድሞች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩና በባሕሩ ውስጥ እንደ ተሻገሩ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ።

2. እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋር ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ።

3. ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤

4. ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ ዐለት ክርስቶስ ነበረ።

5. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ ስላል ተሰኘ በበረሓ ወድቀው ቀሩ።

6. እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ፣ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል።

7. “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ።

8. ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺህ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም።

9. ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን።

10. ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጒረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጒረምርሙ።

11. ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ።

12. ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።

13. በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።

ከጣዖት ጋር አለመተባበር

14. ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።

15. ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ።

16. የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን?

17. እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና።

18. እስቲ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን?

19. ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን?

20. አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋር እንድት ተባበሩም አልሻም።

21. የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም።

22. ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከእርሱ እንበልጣለንን?

የአማኞች ነጻነት

23. “ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉም ነገር ተፈቅዶአል”፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር አያን ጽም።

24. እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ብቻ አይፈልግ።

25. በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ፣ በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ፤

26. ምድርና በውስጧ ያለው ሁሉ የጌታ ነውና።

27. የማያምን ሰው ጋብዞአችሁ ለመሄድ ብትፈልጉ በኅሊና ምርምር ውስጥ ሳትገቡ የቀረበላችሁን ሁሉ ብሉ።

28. ነገር ግን አንዱ፣ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ፣ ይህን ስለ ነገራችሁ ሰውና ለኅሊናችሁ ስትሉ አትብሉ።

29. ይህን የምለውም ስለዚያ ሰው ኅሊና እንጂ ስለ አንተ አይደለም፤ ነጻነቴስ በሌላ ሰው ኅሊና ለምን ይመዘን?

30. ምግቡን በምስጋና የምበላ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን ባመሰገንሁበት ነገር ለምን እወቀሣለሁ?

31. እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።

32. ለአይሁድም ሆነ ለግሪኮች ወይም ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን መሰናክል አትሁኑ፤

33. እኔ ሰውን ሁሉ በማንኛውም ረገድ ለማስደሰት እንደምጥር እናንተም እንዲሁ አድርጉ፤ ብዙዎችም ይድኑ ዘንድ፣ ለራሴ የሚጠቅመውን ሳይሆን፣ ለእነርሱ የሚጠቅመውን እሻለሁና።