ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ናቡከደነፆር በሕልሙ ዛፍ አየ

1. ከንጉሥ ናቡከደነፆር፣ በምድር ሁሉ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ ሰላም ይብዛላችሁ!

2. ልዑል አምላክ ያደረገልኝን ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ እጅግ ደስ እያለኝ ነው።

3. ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው!ድንቁስ እንዴት ብርቱ ነው!መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ግዛቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

4. እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደልቶኝ በቤተ መንግሥቴም ተመችቶኝ እኖር ነበር፤

5. አንድ ያስፈራኝ ሕልም አየሁ፤ በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ፣ ወደ አእምሮዬ የመጡት ምስሎችና ራእዮች አስደነገጡኝ።

6. ስለዚህ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ መጥተው ሕልሜን እንዲተረጒሙልኝ አዘዝሁ።

7. ጠንቋዮቹ፣ አስማተኞቹ፣ ኮከብ ቈጣሪዎቹና መተተኞቹ በመጡ ጊዜ ሕልሙን ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊተረጒሙልኝ አልቻሉም።

8. በመጨረሻም በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገብቶ በፊቴ ቆመ፤ ሕልሜንም ነገርሁት።

9. እኔም እንዲህ አልሁት፤ “የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ ዐውቃለሁ፤ ምንም ዐይነት ምስጢር አያስቸግርህም፤ ያየሁት ሕልም እነሆ፤ ተርጒምልኝ።

10. በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ።

11. ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።

12. ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከእርሱ ይመገብ ነበር።

13. “በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየሁት ራእይ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።

14. እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘ዛፉን ቊረጡ፤ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ ከሥሩ ያሉት እንስሶች፣ በቅርንጫፎቹም ላይ ያሉት ወፎች ይሽሹ።

15. ነገር ግን ጒቶውና ሥሩ በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ።“ ‘በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ በጥሻም ውስጥ ከአራዊት ጋር ይኑር።

16. አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፤ የእንስሳም አእምሮ ይሰጠው፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት።

17. “ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጾአል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሮአል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’

18. “እኔ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፤ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሁሉ አንዳቸውም ሊተረጒሙልኝ ስላልቻሉ፣ ምን ማለት እንደሆነ ንገረኝ። አንተ የአማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጒምልኝ ትችላለህ።

ዳንኤል ሕልሙን ተረጐመ

19. ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ አያስደንግጥህ” አለው።ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጒሙም ለጠላቶችህ!

20. እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣

21. ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጎጆ መሥሪያ ያለው፣

22. ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ።

23. “ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቊረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጒቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንድ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ።

24. “ንጉሥ ሆይ፤ ትርጒሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤

25. ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባትዓመታት ያልፉብሃል።

26. የዛፉ ጒቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለ ስልህ ያመለክታል።

27. ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።”

ሕልሙ ተፈጸመ

28. ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤

29. ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ፣ ንጉሡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ ሳለ፣

30. “በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ።

31. ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ፣ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለ አንተ የታወጀው ይህ ነው፤ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዶአል፤

32. ከሕዝብ መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊት ጋርም ትኖራለህ፤ እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመት ያልፋል።”

33. ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጒሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

34. ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት።ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

35. የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤በሰማይ ኀይላት፣በምድርም ሕዝቦች ላይ፣የወደደውን ያደርጋል፤እጁን መከልከል የሚችል የለም፤‘ምን ታደርጋለህ?’ ብሎ የሚጠይቀውም የለም።

36. አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ፣ ወዲያው ለመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሱልኝ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቴ ፈለጉኝ፤ ወደ ዙፋኔም ተመለስሁ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንሁ።

37. የሰማይ አምላክ የሚያደርገው ሁሉ ትክክል፣ መንገዶቹም ሁሉ ጽድቅ ስለሆኑ፣ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል።