ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳንኤል በባቢሎን እንዲሠለጥን ተደረገ

1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።

2. ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ካሉት ዕቃዎች ከጥቂቶቹ ጋር በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ ወደ አምላኩ ቤት ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ በአምላኩም ግምጃ ቤት ውስጥ አኖራቸው።

3. ከዚያ በኋላ ንጉሡ የቤተ መንግሥቱን ጃንደረቦች አለቃ አስፋኔዝን፣ ከንጉሣዊው ቤተ ሰብና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን እስራኤላውያንን እንዲያመጣ አዘዘው፤

4. እነርሱም የአካል ጒዳት የሌለባቸው መልከ መልካሞች፣ ማንኛውንም ትምህርት የመማር ችሎታ ያላቸው፣ ዕውቀት የሞላባቸው፣ ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉትንና በንጉሡም ቤት ለማገልገል ብቃት ያላቸው ወጣት ወንዶች ናቸው፤ የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እንዲያስተምራቸውም አዘዘው።

5. ንጉሡም በየዕለቱ የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማዕድ ድርጎ እንዲሰጣቸው አደረገ፤ ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ናቸው።

6. ከነዚህም መካከል ከይሁዳ የመጡት ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ፤

7. የጃንደረቦቹ አለቃም አዲስ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያን አብድናጎ ብሎ ጠራቸው።

8. ዳንኤል ግን በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ፤ በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ፈቃድ ጠየቀው።

9. እግዚአብሔርም ለዳንኤል በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ሞገስንና መወደድን ሰጠው።

10. ሆኖም የጃንደረቦቹ አለቃ ለዳንኤል፣ “መብሉንና መጠጡን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ብትታዩ፣ በንጉሡ ዘንድ በራሴ ላይ አደጋ ታስከትሉብኛላችሁ።” ብሎ ነገረው።

11. ዳንኤልም የጃንደረቦቹን አለቃ በዳንኤል፣ በአናንያ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ የሾመውን መጋቢ እንዲህ አለው፤

12. “እባክህ አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ ለመብል ከአትክልት፣ ለመጠጥም ከውሃ በስተቀር ምንም አይሰጠን፣

13. ከዚያም የእኛን መልክና የንጉሡን መብል የሚበሉትን ወጣቶች መልክ አስተያይ፤ በአገልጋዮችህ ላይ የወደድኸውን አድርግብን።”

14. እርሱም በዚህ ነገር ተስማማ፤ ለዐሥር ቀንም ፈተናቸው።

15. ከዐሥር ቀን በኋላም የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ።

16. ስለዚህ መጋቢው ምርጥ የሆነውን ምግባቸውንና ሊጠጡት የሚገባውን የወይን ጠጅ አስቀርቶ በምትኩ አትክልት ሰጣቸው።

17. እግዚአብሔር ለእነዚህ አራት ወጣቶች በማንኛውም ሥነ ጽሑፍና ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፣ ዳንኤልም ማንኛውንም ራእይና ሕልም የመረዳት ችሎታ ነበረው።

18. ወደ እርሱ እንዲመጡ ንጉሡ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ፣ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር አቀረባቸው፤

19. ንጉሡም ባነጋገራቸው ጊዜ ከመካከላቸው እንደ ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ያለ ከቶ አልተገኘም፤ ስለዚህ በንጉሡ አገልግሎት ላይ ተሰማሩ።

20. ንጉሡ በጠየቃቸው በማንኛውም የጥበብና የማስተዋል ጒዳይ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኞችና ድግምተኞች ሁሉ ዐሥር እጅ በልጠው አገኛቸው።

21. ዳንኤልም፣ ንጉሥ ቂሮስ እስከ ነገሠበት እስከ መጀመሪያው ዓመት ድረስ እዚያው ቈየ።