ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የመጨረሻ ዘመን

1. “በዚያን ዘመን ስለ ሕዝብህ የሚቈመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል። መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ስማቸው በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ ይድናሉ።

2. በምድር ዐፈር ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹም ለውርደትና ለዘላለም ጉስቍልና ይነሣሉ።

3. ጥበበኞች እንደ ሰማይ ጸዳል፣ ብዙዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።

4. ዳንኤል ሆይ፤ አንተ ግን፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የመጽሐፉን ቃል ዝጋ፤ አትመውም። ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል።

5. እኔም ዳንኤል ተመለከትሁ፤ እነሆ ከፊት ለፊቴ ሌሎች ሁለት ቆመው ነበር፤ አንዱ ከወንዙ በዚህኛው ዳር፣ ሌላው ደግሞ ከወንዙ በዚያኛው ዳር።

6. ከእነርሱም አንዱ፣ ከወንዙ ውሃ በላይ የነበረውንና በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ሊፈጸሙ ምን ያህል ጊዜ ይቀራል?” አለው።

7. ከወንዙ ውሃ በላይ የነበረው በፍታ የለበሰው ሰው፣ ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፣ “ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመንም እኩሌታ ይሆናል፤ የተቀደሰው ሕዝብ ኀይል መሰበር ሲያከትም፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይፈጸማሉ” ብሎ ለዘላለም በሚኖረው በእርሱ ሲምል ሰማሁ።

8. እኔም ሰማሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም፤ ስለዚህ፣ ጌታዬ ሆይ፤ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ።

9. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ ቃሉ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ስለ ሆነ ሂድ፤

10. ብዙዎች ይነጻሉ፤ ይጠራሉ፤ እንከን አልባም ይሆናሉ፤ ክፉዎች ግን በክፋታቸው ይጸናሉ፤ ከክፉዎች አንዳቸውም አያስተውሉም፤ ጠቢባን ግን ያስተውላሉ።

11. “የዘወትሩ መሥዋዕት ከተቋረጠበትና ጥፋትን የሚያመጣው የጥፋት ርኵሰት ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል።

12. የሚታገሥና እስከ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀን ፍጻሜ የሚደርስ የተባረከ ነው።

13. “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ።”