ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 19:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በድንጋይ ይወገራል ወይም በቀስት ይወጋል፤ ምንም እጅ በእርሱ ላይ አያርፍም፤ ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ወደ ተራራው መውጣት የሚችሉት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት በተነፋ ጊዜ ብቻ ነው።

14. ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ከሄደ በኋላ ቀደሳቸው፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።

15. ከዚያም ለሕዝቡ፣ “ለሦስተኛው ቀን ራሳችሁን አዘጋጁ፤ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ ተቈጠቡ” አላቸው።

16. በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጎድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ።

17. ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ለማገናኘት ሕዝቡን ከሰፈር ይዞ ወጣ፤ ከተራራውም ግርጌ ቆሙ።

18. የሲና ተራራ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስለወረደበት በጢስ ተሸፍኖ ነበር። ጢሱ ከምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ወደ ላይ ተትጐለጐለ፤ ተራራውም በሙሉ በኀይል ተናወጠ።

19. የመለከቱም ድምፅ እያየለ መጣ። ከዚያም ሙሴ ተናገረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በድምፅ መለሰለት።

20. እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ወረደ፤ ሙሴን ወደ ተራራው ጫፍ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።

21. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለማየት በመጣደፍ ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ውረድና አስጠንቅቃቸው

22. ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርቡት ካህናት እንኳ ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው፤ አለዚያ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣውን ያወርድባቸዋል።”

23. ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ሊወጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም አንተ ራስህ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ የተቀደሰም በማድረግ ለየው’ በማለት አስጠንቅቀኸናልና።”

24. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ውረድና አሮንን ከአንተ ጋር ይዘኸው ውጣ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለመምጣት መጣደፍ የለባቸውም፤ አለዚያ እርሱ ቍጣውን ያወርድባቸዋል።”

25. ስለዚህ ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 19