ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 4:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ከዚህም በላይ ይህች ከተማ ከተሠራች፣ ቅጥሮቿም እንደ ገና ከተገነቡ፣ ቀረጥና እጅ መንሻ ወይም ግብር እንደማይከፍሉ፣ የቤተ መንግሥቱም ገቢ እንደሚቀንስ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን።

14. አሁንም እኛ ስለ ቤተ መንግሥቱ ስለሚገደን፣ የንጉሡም ክብር ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፣ ይህ ነገር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ይህን መልእክት ልከናል፤

15. ስለዚህ በአባቶችህ ቤተ መዛግብት ምርመራ ይደረግ፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ይህች ከተማ ዐመፀኛ ከተማ እንደሆነች፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የጐዳችና ከጥንት ጀምሮ የዐመፅ ጐሬ ስለ መሆኗ ማስረጃ ታገኛለህ፤ እንግዲህ ከተማዪቱ የተደመሰሰችው በዚህ ምክንያት ነው።

16. ይህች ከተማ ተመልሳ የምትሠራና ቅጥሮቿም እንደ ገና የሚገነቡ ከሆነ፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ምንም ነገር እንደማ ይኖርህ ንጉሥ ታውቅ ዘንድ እንወዳለን።

17. ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤ለአገረ ገዡ ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤ሰላም ለእናንተ ይሁን፤

18. የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጒሞ ተነቧል።

19. እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጎአል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደሆነች ማስረጃ ተገኝቶአል።

20. ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት።

21. አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ።

22. ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሣራ ለምን እየበዛ ይሄዳል?

23. የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው።

24. ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 4