ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቤተ መቅደሱ እንዳይሠራ የተነሣ ተቃውሞ

1. የይሁዳና የብንያም ጠላቶች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሲሰሙ፣

2. ወደ ዘሩባቤልና ወደ ቤተ ሰቡ አለቆች መጥተው፣ “እኛም እንደ እናንተ አምላካችሁን የምንፈልግ ነን፤ የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ጊዜ ጀምሮ ለእርሱ ስንሠዋለት ቈይተናል፤ ስለዚህ አብረን ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሏቸው።

3. ዘሩባቤል፣ ኢያሱና ሌሎቹ የእስራኤል ቤተ ሰቦች አለቆች ግን፣ “ለአምላካችን ቤተ መቅደስ እንድትሠሩ ከእኛ ጋር የሚያገናኛችሁ ምንም ነገር የለም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ባዘዘን መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የምንሠራው እኛ ብቻ ነን” ሲሉ መለሱላቸው።

4. ከዚያም የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ።

5. ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ዕቅዶቻቸውን የሚያሰናክሉ መካሪዎችን በገንዘብ ገዙባቸው።

በጠረክሲስና በአርጤክስስ ዘመን የተደረገ ሌላው ተቃውሞ

6. በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው።

7. በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትሪዳጡ፣ ጣብኤልና ተባባሪዎቹ ወደ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤው የተጻፈው በአረማይስጥ ፊደል፣ በአረማይስጥ ቋንቋ ነበረ።

8. አገረ ገዡ ሬሁምና ጸሓፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፤

9. ደብዳቤው የተጻፈው፣ ከአገረ ገዡ ሬሁም፣ ከጸሓፊው ሲምሳይ በትሪፖሊስ፣ በፋርስ፣ በአርክ፣ በባቢሎን፣ እንዲሁም በሱሳ ማለትም በኤላማውያን ላይ ዳኞችና ገዦች ከሆኑት ከተባባሪዎቻቸው፣

10. ደግሞም ታላቁና ኀያሉ አስናፈር አፍልሶ በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ሌሎች ሕዝቦች ነው።

11. የላኩለት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤ለንጉሥ አርጤክስስ፣በኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚኖሩት አገልጋዮችህ የተላከ፤

12. ከአንተ ዘንድ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ዐመፀኛና ርኵስ ከተማ እንደ ገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጥሮቿንም እንደ ገና በመሥራትና መሠረቶቿንም በመጠገን ላይ መሆናቸው በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን።

13. ከዚህም በላይ ይህች ከተማ ከተሠራች፣ ቅጥሮቿም እንደ ገና ከተገነቡ፣ ቀረጥና እጅ መንሻ ወይም ግብር እንደማይከፍሉ፣ የቤተ መንግሥቱም ገቢ እንደሚቀንስ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን።

14. አሁንም እኛ ስለ ቤተ መንግሥቱ ስለሚገደን፣ የንጉሡም ክብር ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፣ ይህ ነገር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ይህን መልእክት ልከናል፤

15. ስለዚህ በአባቶችህ ቤተ መዛግብት ምርመራ ይደረግ፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ይህች ከተማ ዐመፀኛ ከተማ እንደሆነች፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የጐዳችና ከጥንት ጀምሮ የዐመፅ ጐሬ ስለ መሆኗ ማስረጃ ታገኛለህ፤ እንግዲህ ከተማዪቱ የተደመሰሰችው በዚህ ምክንያት ነው።

16. ይህች ከተማ ተመልሳ የምትሠራና ቅጥሮቿም እንደ ገና የሚገነቡ ከሆነ፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ምንም ነገር እንደማ ይኖርህ ንጉሥ ታውቅ ዘንድ እንወዳለን።

17. ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤ለአገረ ገዡ ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤ሰላም ለእናንተ ይሁን፤

18. የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጒሞ ተነቧል።

19. እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጎአል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደሆነች ማስረጃ ተገኝቶአል።

20. ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት።

21. አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ።

22. ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሣራ ለምን እየበዛ ይሄዳል?

23. የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው።

24. ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ።