ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሰሜን ነገሥታት ድል መሆን

1. የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ማዶን ንጉሥ፣ ወደ ዮባብ ንጉሥ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አዚፍ ንጉሥ ላከ፤

2. እንዲሁም በተራራማው አገር ከኪኔሬት ደቡብ በዓረባ፣ በምዕራቡ ቈላ አገርና ከዶር ኰረብታ በስተ ምዕራብ ወዳሉት ነገሥታት ላከ፤

3. ደግሞም በምሥራቅና በምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያንና በኰረብታማው አገር ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን፣ እንዲሁም ደግሞ በምጽጳ ምድር በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ወዳሉት ወደ ኤዊያውያን ነገሥታት መልእክት ላከ።

4. እነዚህም ሰራዊታቸውን ሁሉ እጅግ ብዙ ከሆኑ ፈረሶችና ሠረገሎች ጋር ይዘው ወጡ፤ የሰራዊቱም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበር።

5. እነዚህ ሁሉ ነገሥታት እስራኤልን ለመውጋት ኀይላቸውን አስተባብረው በማሮን ውሃ አጠገብ በአንድነት ሰፈሩ።

6. እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነዚህን ሁሉ ነገ በዚች ሰዓት እንደ ሙት አድርጌ፣ በእስራኤል እጅ አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም ታቃጥላለህ” አለው።

7. ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውሃ መጥተው ወጓቸው።

8. እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ስለሰጣቸው ድል አደረጓቸው፤ በታላቂቱ ሲዶና መንገድ መጨረሻ እስከ ማስሮን፣ በስተ ምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዷቸው፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።

9. ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም አቃጠለ።

10. በዚያን ጊዜም ኢያሱ ወደ ኋላ ተመልሶ አጾርን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለው፤ አጾርም ቀድሞ በእነዚህ ሁሉ መንግሥታት ላይ የበላይነት ነበራት።

11. በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድ እንኳ ሳያስቀሩ ሁሉንም ደመሰሱ፤ ራሷን አሦርንም በእሳት አቃጠሏት።

12. ኢያሱ እነዚህን የነገሥታት ከተሞች በሙሉና ነገሥታታቸውን ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም ስለት ፈጃቸው፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ ደመሰሳቸው።

13. ያም ሆኖ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአጾር በስተቀር፣ እስራኤላውያን በየተራራው ላይ ያሉትን ከተሞች አላቃጠሉም ነበር።

14. እስራኤላውያን ምርኮውን በሙሉ፣ ከእነዚህም ከተሞች የተገኙትን እንሰሳት ለራሳቸው ወሰዱ፤ ሕዝቡን ግን በሙሉ በሰይፍ ስለት ፈጁት፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድም ሳያስቀሩ ፈጽመው ደመሰሱት።

15. እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ፣ ሙሴም ኢያሱን አዘዘው፤ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ እርሱ ያልፈጸመው አንዳች ነገር አልነበረም።

16. ኢያሱ ያንን ምድር በሙሉ ማለት ተራራማውን አገር፣ ኔጌቭን ሁሉ፣ የጎሶምን ምድር በሙሉ፣ የምዕራቡን ቈላ፣ ዓረባን እንዲሁም የእስራኤልን አገር ደጋውንና ቈላውን ጠቅልሎ ያዘ፤

17. እንዲሁም እስከ ሴይር በሚደርሰው ከሐላቅ ተራራ አንሥቶ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስ ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ያዘ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ ያዘ፤ መትቶም ገደላቸው።

18. ኢያሱ ከእነዚህ ነገሥታት ጋር ብዙ ዘመን የፈጀ ጦርነት አደረገ።

19. በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በስተቀር፣ ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ውል ያደረገ አንድም ከተማ አልነበረም፤ ሁሉንም የያዙት በጦርነት ነው።

20. እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ያለ አንዳች ርኅራኄ ፈጽሞ ይደመስሳቸው ዘንድ እስራኤልን እንዲወጉ ልባቸውን ያደነደነው ራሱ እግዚአብሔር ነውና።

21. በዚያን ጊዜ ኢያሱ ሄዶ በተራራማው አገር ማለት በኬብሮን፣ በዳቤርና በአናብ እንዲሁም በመላው የይሁዳና የእስራኤል ተራራማ አገሮች ያሉትን የዔናቅን ዘሮች ከነከተሞቻቸው በሙሉ ደመሰሳቸው፤

22. ከእነዚህም ጥቂቶቹ ብቻ በጋዛ፣ በጌትና በአሽዶድ ሲቀሩ፣ በእስራኤል የቀሩ የዔናቅ ዘሮች ግን አልነበሩም።

23. ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን በሙሉ ያዘ፤ እንደ ነገዳቸው አከፋፈል በመመደብም ርስት አድርጎ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው።ከዚያም ምድርቱ ከጦርነት ዐረፈች።