ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ቃል ኪዳኑ በሴኬም ታደሰ

1. ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ በሴኬም ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምት ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ።

2. ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ፣ የአብርሃምንና የናኮርን አባት ታራን ጨምሮ ከብዙ ዘመን በፊት ከወንዙ ማዶ ኖሩ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ።

3. እኔ ግን አባታችሁን አብርሃምን ከወንዙ ማዶ ካለው ምድር አምጥቼ፣ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሮቹን አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት።

4. ለይስሐቅ ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም ኰረብታማውን የሴይርን ምድር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብና ልጆቹ ግን ወደ ግብፅ ወረዱ።

5. “ ‘ከዚያም ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ባመጣሁት መቅሰፍት ግብፃውያንን አስጨንቄ፣ እናንተን ከዚያ አወጣኋችሁ።

6. አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ወደ ባሕሩ መጣችሁ፤ ግብፃውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ተከታተሏቸው።

7. እነርሱ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረገ። ባሕሩን በላያቸው አመጣ፤ አሰጠማቸውም። በግብፃውያን ላይ ያደረግሁትንም ራሳችሁ በዐይናችሁ አያችሁ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ኖራችሁ።

8. “ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ።

9. የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ፣ እስራኤልን ለመውጋት ተነሣ፣ እናንተንም መጥቶ ይረግማችሁ ዘንድ ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም መልእክተኛ ላከ፤

10. እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግሁም፤ ስለዚህ ደግሞ ደጋግሞ መረቃችሁ፤ እኔም፤ ከባላቅ እጅ ታደግኋችሁ።

11. “ ‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን እንደ ወጓችሁ ሁሉ፤ የኢያሪኮም ነዋሪዎች ወጓችሁ።

12. በፊታችሁ ተርብ ላክሁ፤ ይህም እነርሱንና ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ጭምር ከፊታችሁ አሳደደ፤ ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሰይፍና ቀስት ያደረጋችሁት አይደለም።

13. ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድርና ያልሠራችኋቸውን ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፣ በከተሞቹ ትኖራላችሁ፤ ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ ትበላላችሁ።’

14. “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት። የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብፅ ያመለኳቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ።

15. እግዚአብሔርን ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”

16. ከዚያም ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሌሎችን አማልእክት ለማምለክ ብለን እግዚአብሔርን መተው ከእኛ ይራቅ።

17. እኛንና የቀደሙ አባቶቻችንን ከዚያ ከጦርነት ምድር ከግብፅ ያወጣን፣ በፊታችንም እነዚያን ታላላቅ ምልክቶች ያደረገ ማነው? ራሱ አምላካችን እግዚአብሔር አይደለምን? በጒዞአችን ላይና ባለፍንባቸውም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የጠበቀን እርሱ ነው።

18. እንዲሁም እግዚአብሔር በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ጨምሮ ሕዝቦችን ሁሉ ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ አምላካችን ነውና።”

19. ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ እርሱ ቅዱስ አምላክና፤ ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ዐመፃችሁን ወይም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም።

20. እግዚአብሔርን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን የምታመልኩ ከሆነ፣ መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችኋልም።”

21. ሕዝቡ ግን ኢያሱን፣ “የለም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት።

22. ከዚያም ኢያሱ፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ መርጣችኋልና በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው።እነርሱም፣ “አዎን ምስክሮች ነን” ሲሉ መለሱ።

23. ኢያሱም፣ “እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር መልሱ” አላቸው።

24. ሕዝቡም ኢያሱን፣ “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” አሉት።

25. በዚያን ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የሚመሩበትንም ደንብና ሥርዐት እዚያው ሴኬም ሰጣቸው።

26. ኢያሱም እነዚህን ቃሎች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ በባሉጥ ዛፍ ሥር፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ አጠገብ አቆመው።

27. ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ፣ “እነሆ፤ ይህ ድንጋይ፣ እግዚአብሔር የተናገረንን ሁሉ ሰምቶአል፣ በእኛም ይመሰክርብናል፤ እናንተም በአምላካችሁ ዘንድ እውነተኞች ሆናችሁ ባትገኙ ምስክር ይሆንባችኋል” አላቸው።

ኢያሱ በተሰፋዪቱ ምድር ተቀበረ

28. ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ ወደየርስቱ እንዲሄድ አሰናበተ።

29. ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ።

30. በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው፣ ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት በተምናሴራ ቀበሩት።

31. ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ከኢያሱም በኋላ በሕይወት በኖሩትና እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አመለኩ።

32. እስራኤላውያን ከግብፅ ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም፣ ያዕቆብ ከሰኬም አባት ከኤሞር በመቶ ሰቅል ብር በገዛው በሴኬም ምድር ተቀበረ፤ ይህችም የዮሴፍ ዘሮች ርስት ሆነች።

33. እንዲሁም የአሮን ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በሚገኘው ለልጁ ለፊንሐስ በዕጣ በደረሰው በጊብዓ ምድር ተቀበረ።