ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 32:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ንጉሡም እንደዚሁ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በመሳደብ፣ “የሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች አማልክት፣ ከእጄ እንዳልታደጉ ሁሉ፣ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም” ሲል በእርሱ ላይ ደብዳቤ ጻፈ።

18. ከዚያም በማስደንገጥና በማስፈራራት ከተማዪቱን ለመያዝ ሲሉ በቅጥሩ ላይ ወደተቀመጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በዕብራይስጥ ቋንቋ ጮኹ፤

19. የሰው እጅ በሠራቸው በሌሎች የምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደ ተናገሩት ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ።

20. ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ስለዚህ ጒዳይ በጸሎት ወደ ሰማይ ጮኹ።

21. እግዚአብሔርም መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር ተዋጊዎችን፣ መሪዎችንና የጦር መኮንኖችን እንዲያጠፋቸው አደረገ። ስለዚህ ንጉሡ በውርደት ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩ ቤተ ጣዖት እንደ ገባም፣ የገዛ ወንዶች ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።

22. እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬምና ከሌሎችም እጅ ሁሉ አዳናቸው፤ በዙሪያቸው ካሉትም ሁሉ ጠበቃቸው፤

23. ብዙዎችም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ውድ የሆኑ ገጸ በረከቶች አመጡለት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።

24. በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው።

25. የሕዝቅያስ ልብ ግን ታበየ እንጂ ስለ ተደረገለት በጎ ነገር ተገቢ ምላሽ አልሰጠም፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ።

26. ይሁን እንጂ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ልባቸው ትዕቢት ራሳቸውን አዋረዱ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በዘመነ መንግሥቱ አልመጣባቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 32