ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 12:11-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።

12. አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።’ ”

13. ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤

14. ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”

15. ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፣ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን እግዚአብሔር ከባድ ሕመም ላይ ጣለው።

16. ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ በተከታታይ ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ።

17. የቤተ ሰው ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያስነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ነገር አልበላም።

18. በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፣ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጒዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ።

19. ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፣ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “አዎን ሞቶአል” ብለው መለሱለት።

20. በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ።

21. አገልጋዮቹም፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት።

22. እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፣ ‘እግዚአብሔር ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ።

23. አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፣ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፣ እርሱ ወደ እኔ አይመለስ!”

24. ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። እግዚአብሔርም ወደደው፤

25. እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 12