ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ

1. ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ላይ አንድ ነገር ደረሰ፤ ቦታውም በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያ ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር።

2. አክዓብም ናቡቴን፣ “የወይን ተክል ቦታህ ከቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ፣ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልኝ፤ በምትኩ ከዚህ የበለጠ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ የተሻለ ሆኖ ከታየህም የሚያወጣውን ገንዘብ እከፍልሃለሁ” አለው።

3. ናቡቴ ግን፣ “ዐፅመ ርስቴን እለቅልህ ዘንድ እግዚአብሔር አይበለው” ሲል መለሰለት።

4. ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።

5. ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።

6. እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።

7. ሚስቱ ኤልዛቤልም፣ “አንተ አሁን የእስራኤል ንጉሥ ትባላለህ? በል ተነሥና እህል ቅመስ፤ ደስም ይበልህ፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እኔ እንድታገኝ አደርግሃለሁ” አለችው።

8. ስለዚህ በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጻፈች፤ በገዛ ማኅተሙም አትማ በናቡቴ ከተማ አብረውት ለሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት ላከች።

9. በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፤“የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀምጡት።

10. እንዲሁም ሁለት የሐሰት ምስክሮች ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና፣ ‘እግዚአብሔርንም ንጉሡንም ሰድቦአል’ ብለው ይመስክሩበት፤ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት።”

11. ስለዚህ በናቡቴ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት በደብዳቤዎቹ ላይ እንደ ጻፈችላቸው አደረጉ።

12. የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀመጡት።

13. ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት።

14. ከዚያም ለኤልዛቤል፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል” ብለው ላኩባት።

15. ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቶአል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው።

16. አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።

17. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

18. “ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል።

19. እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ? ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”

20. አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ።

21. ‘እነሆ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ዘርህን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ እያንዳንዱን የአክዓብን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ከእስራኤል እጠርጋለሁ።

22. ለቊጣ ስላነሣ ሣኸኝና እስራኤልንም ስላሳትሃቸው ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።’

23. “ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር፣ ‘በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ውሾች ኤልዛቤልን ይበሏታል’ ይላል።

24. “ደግሞም ከአክዓብ ወገን ሆኖ በከተማ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በገጠር የሞተውንም የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”

25. በሚስቱ በኤልዛቤል ተገፋፍቶ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራሱን የሸጠ እንደ አክዓብ ያለ ሰው ከቶ አልነበረም።

26. እግዚአብሔር ከእስራኤል ፊት ያሳደዳቸው አሞራውያን እንዳደረጉት ሁሉ፣ እርሱም ጣዖታትን በማምለክ እጅግ የሚያስጸይፍ ርኵሰት ፈጸመ።

27. አክዓብም ይህን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶ፤ ጾመ፤ በማቅ ላይ ተኛ በሐዘን ኵርምት ብሎም ይሄድ ነበር።

28. ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ፤

29. አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን? ራሱን ስላዋረደ ይህን መከራ በዘመኑ አላመጣበትም፤ ነገር ግን ይህን በቤቱ ላይ የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።”