ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ

1. ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ለማምጣት፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ እርሱ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ጠራቸው።

2. በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ።

3. የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜም ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤

4. የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ይህን ሁሉ ተሸከሙ።

5. ንጉሥ ሰሎሞንና አብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤም በታቦቱ ፊት በመሆን ስፍር ቊጥር የሌለው በግና በሬ ሠዋ።

6. ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወዳለው ማደሪያው፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማስገባት ከኪሩቤል ክንፍ በታች አኖሩት።

7. ኪሩቤልም ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ክንፋቸውን ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ።

8. መሎጊያዎቹ ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከመቅደሱ ሆኖ ይታዩ ነበር፤ ከመቅደሱ ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ።

9. የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ኪዳን በገባበት በኮሬብ፣ ሙሴ በታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም።

10. ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው።

11. የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ካህናቱ በደመናው ምክንያት አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም ነበር።

12. ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሮአል፤

13. እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።”

14. መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ።

15. ከዚያም እንዲህ አለ፤“ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤

16. ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠ ራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’

17. “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤

18. እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስበሃልና፣ ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፤

19. ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ ሳትሆን፣ ከአንተ የሚወለደው ልጅህ ነው፤ አዎን ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው።’

20. “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ፈጽሞአል፤ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቻለሁ፤ በእስራኤል ዙፋን ተቀምጫለሁ፤ እንዲሁም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ።

21. ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”

ሰሎሞን በምረቃው ላይ ያቀረበው ጸሎት

22. ከዚያም ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ፣

23. እንዲህ አለ፤“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በፍጹም ልባቸው ጸንተው ለሚኖሩ አገልጋዮችህ ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ጽኑ ፍቅርህን የምትገልጥ አንተ ነህ፤ በላይ በሰማይ፣ በታችም በምድር እንዳንተ ያለ አምላክ ከቶ የለም፤

24. ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ ጠብቀሃል፤ በአፍህ ተናገርህ፤ ይህንኑም በዛሬው ዕለት በእጅህ ፈጸምኸው።

25. “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ለአባቴ ለባሪያህ ለዳዊት፣ ‘አንተ እንዳደረግኸው ሁሉ፣ ልጆችህ በፊቴ ለመመላለስ በሚያደርጉት ሁሉ ይጠንቀቁ ብቻ እንጂ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው አታጣም’ ስትል የሰጠኸውን ተስፋ ፈጽምለት።

26. አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

27. “ነገር ግን አምላክ በእርግጥ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ!

28. አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህም ሆኖ የባሪያህን ጸሎትና ልመና ስማ፤ በዛሬው ዕለት ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ልመና አድምጥ።

29. ባሪያህ ወደዚህ ቦታ የሚያቀርበውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ወዳልኸው በዚህ ስፍራ ወዳለው ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ።

30. ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ልመናቸውን ተቀበል፤ መኖሪያህ በሆነው በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

31. “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ መማል ኖሮበት ቢመጣና በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣

32. ይህን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ፤ ለበደለኛው ስለ አድራጎቱ የእጁን ክፈል፤ ከበደል ነጻ ለሆነውም ንጽሕናውን ይፋ በማድረግ ይህንኑ አረጋግጥለት።

33. ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ በጠላቶቻቸው ድል በሚሆኑበት ጊዜ፣ ወደ አንተም ተመልሰው ስምህን ቢጠሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩና ልመናቸውን ቢያቀርቡ፣

34. በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህ የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሰህ አግባቸው።

35. “ሕዝቡም አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከበደላቸው ቢመለሱ፣

36. በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ ለሰጠሃትም ምድር ዝናብ አውርድ።

37. “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት፣ ዋግ ወይም አረማሞ በሚከሠትበት፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚወርድበት ወይም በምድራቸው ውስጥ ባሉት ከተሞቻቸው ጠላት ቢከባቸው እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚመጣባቸው ጊዜ፣

38. ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንኛውም ሰው የልቡን ጭንቀት ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣

39. በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። አንተ ብቻ የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ሁሉ ክፈለው፤

40. ይህም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ አንተን እንዲፈሩ ነው።

41. “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፣

42. ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፣

43. አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የጠየቀህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ ስምህን ዐውቀው፣ ሕዝብህ እስራኤል አንተን እንደሚፈሩት ሁሉ እንዲፈሩህ፣ እኔ የሠራሁትም ይህ ቤት በስምህ መጠራቱን እንዲያውቁ ነው።

44. “ሕዝብህ ጠላታቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ወደ የትኛውም ቦታ ለጦርነት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ከተማና እኔ ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፣

45. ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ርዳቸውም።

46. “መቼም ኀጢአት የማይሠራ የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ አንተም ተቈጥተህ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነው ምድሩ ማርኮ ለሚወስደው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣

47. ተማርከው በሚኖሩበት አገር ሳሉ ልባቸው ቢመለስ፣ በተማረኩበትም ምድር ሆነው ንስሓ ቢገቡና ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣

48. እንዲሁም ማርከው በወሰዷቸው ጠላቶቹ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፣ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደዚህች ምድር ወደ መረጥሃትም ወደዚህች ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፣

49. ከማደሪያህ ከሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ ልመናቸውንም ተቀበል፤ ርዳቸውም።

50. በአንተ ላይ ስለሠሩት ኀጢአት፣ አንተንም ስለ በደሉህ በደል ሁሉ ሕዝብህን ይቅር በል፤ የማረኳቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ።

51. ከዚያች እንደ ብረት ማቅለጫ እቶን እሳት ከሆነችው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህም ርስትህም ናቸውና።

52. “አሁንም ዐይኖችህ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና የተከፈቱ ይሁኑ፤ ወደ አንተ በሚጮኹበትም ጊዜ ሁሉ ስማቸው፤

53. አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ፣ በባሪያህ በሙሴ አማካኝነት እንደ ተናገርኸው ሁሉ፣ ርስትህ ይሆኑ ዘንድ ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ለይተሃቸዋልና።”

54. ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ጸሎትና ልመና ለእግዚአብሔር አቅርቦ ከፈጸመ በኋላ፣ እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፣ በጒልበቱ ተንበርክኮ ከነበረበት ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ።

55. ከዚያም ቆሞ መላውን የእስራኤልን ጉባኤ ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ ሲል መረቀ፤

56. “በሰጠው ተስፋ መሠረት ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን ለሰጠ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ በባሪያው በሙሴ አማካይነት ከተሰጠው መልካም ተስፋ ሁሉ አንድም ቃል አልቀረምና።

57. አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ፣ ከእኛም ጋር ይሁን፤ አይተወን፤ አይጣለንም።

58. በመንገዱም ሁሉ እንድንሄድ፣ ለአባቶቻችን የሰጣቸውን ትእዛዞች፣ ሥርዐቶችና ደንቦች እንድንጠብቅ ልባችንን ወደ እርሱ ይመልስ።

59. በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ።

60. ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆነና ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው።

61. ስለዚህ እንደ ዛሬው ዕለት ሁሉ፣ በሥርዐቱ እንድትኖሩና ትእዛዙን እንድትጠብቁ ልባችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተገዛ ይሁን።”

የቤተ መቅደሱ መመረቅ

62. ከዚያም ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያሉት እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ።

63. ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺህ በግና ፍየል የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ንጉሡና እስራኤላውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ።

64. በዚያኑ ዕለትም ንጉሡ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከለኛ ክፍል ቀደሰ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ አቀረበ፤ ይህን ያደረገውም በእግዚአብሔር ፊት የነበረው የናስ መሠዊያ ከትንሽነቱ የተነሣ የሚቃጠለውን መሥዋዕት የእህሉን ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ መያዝ ባለመቻሉ ነበር።

65. በዚያን ጊዜም ሰሎሞን አብረውት ካሉት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር፣ ማለትም ከሐማት መተላለፊያ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ ካለው ምድር ከተሰበሰበው ታላቅ ጉባኤ ጋር በዓሉን አከበረ። እነርሱም ሰባት ቀን፣ በተጨማሪም ሌላ ሰባት ቀን በድምሩ ዐሥራ አራት ቀን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በዓሉን አከበሩ።

66. በሚቀጥለው ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም ንጉሡን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት በማድረግ ወደየቤታቸው ተመለሱ።