ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከይሁዳ የመጣ የእግዚአብሔር ሰው

1. ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ቃል ታዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ።

2. መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነዳል።’ ”

3. በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔር የሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈሳል’ ” የሚል ነው።

4. ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም

5. እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ።

6. ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች።

7. ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው።

8. የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም።

9. በእግዚአብሔር ቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።”

10. ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ።

11. በዚያን ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት የእግዚአብሔር ሰው እዚያ ያደረገውን ሁሉና ንጉሡንም ምን እንዳለው ለአባታቸው ነገሩት።

12. አባታቸውም፣ “ለመሆኑ የተመለሰው በየትኛው መንገድ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፤ ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የተመለሰበትን መንገድ ለአባታቸው አሳዩት።

13. ስለዚህም ልጆቹን፣ “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነርሱም አህያውን ጫኑለትና ተቀምጦበት

14. እየጋለበ ያን የእግዚአብሔር ሰው ተከተለው። ከዚያም በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና፣ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

15. ስለዚህ ነቢዩ፣ “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው።

16. የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ በዚህ ቦታም አብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤

17. ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው።

18. ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።

19. ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው አብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም።

20. በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤

21. ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዛት አልጠበቅህም፤

22. ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው።

23. የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት።

24. ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር።

25. በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ።

26. ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ።

27. ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት።

28. ከዚያም ሄዶ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ አንበሳውና አህያው በአጠገቡ ቆመው አገኘ፤ አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም አልሰበረውም።

29. ስለዚህ፣ ነቢዩ የዚያን የእግዚአብሔር ሰው ሬሳ አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነ፤ አልቅሶ ለመቅበርም ራሱ ወደሚኖርበት ከተማ አመጣው።

30. ከዚያም ሬሳውን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ “አወይ ወንድሜን” እያሉም አለቀሱለት።

31. ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እኔም በምሞትበት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ ዐጥንቶቼንም በዐጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ።

32. በቤቴል ባለው መሠዊያ፣ በሰማርያ ከተሞችና በየኰረብታው ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል ጮኾ ያሰማው መልእክት በትክክል የሚፈጸም ነውና።”

33. ይህም ሁሉ ሆኖ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ አልተመለሰም፤ ይልቁንም በኰረብታ ማምለኪያዎች ከየትኛውም ክፍል እንደ ገና ካህናትን ይሾም ጀመር፤ ካህን ለመሆን የሚፈልገውንም ሁሉ ለየኰረብታ ማምለኪያዎቹ ለየ።

34. ይህም ኀጢአት የኢዮርብዓም ቤት እንዲወድቅና ከምድር ገጽም እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ።