ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የሰሎሞን ሚስቶች

1. ንጉሥ ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን ማለትም ሞዓባውያትን፣ አሞናውያትን፣ ኤዶማውያትን፣ ሲዶናውያትን፣ ኬጢያውያትን አፈቀረ።

2. እነዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን፣ “ልባችሁን ወደ አማልክታቸው በርግጥ ይመልሱታልና ከእነርሱ ጋር መጋባት የለባችሁም” ካላቸው አሕዛብ ወገን ነበሩ፤ ሆኖም ሰሎሞን ከእነዚሁ ጋር ፍቅሩ ጠና።

3. እርሱም ከነገሥታት የተወለዱ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።

4. ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

5. ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ።

6. ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።

7. ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራ ላይ ለአስጸያፊው የሞዓብ አምላክ ለካሞሽ እንዲሁም አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ማምለኪያ ኰረብታ ሠራ።

8. ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑና መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ለሌሎቹ ሚስቶቹም ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሠራላቸው።

9. ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡ ስለሸፈተ፣ እግዚአብሔር ተቈጣው።

10. ምንም እንኳ ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል ሰሎሞንን ቢከለክለውም፣ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤

11. ስለዚህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ይህን በማድረግህ ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤

12. ይህን ግን ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በዘመንህ አላደርገውም፤ መንግሥትህን የምቀዳት ከልጅህ እጅ ነው።

13. ይህም ሆኖ መንግሥቱን በሙሉ አልነጥቀውም፤ ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”

የሰሎሞን ጠላቶች

14. እግዚአብሔር ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተ ሰብ ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰሎሞን ላይ አስነሣው።

15. ከዚያ በፊት ዳዊት ከኤዶም ጋር በተዋጋ ጊዜ፣ የሞቱትን ለመቅበር መጥቶ የነበረው የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብ የኤዶምን ሰዎች ሁሉ ፈጅቶ ነበር።

16. ኢዮአብና እስራኤላውያን ሁሉ፣ በኤዶም ያሉትን ወንዶች በሙሉ እስኪያጠፉ ድረስ፣ እዚያው ስድስት ወር ቈይተው ነበርና።

17. ሃዳድ ግን ገና በልጅነቱ አባቱን ካገለገሉ ጥቂት ኤዶማውያን ጋር ወደ ግብፅ ሸሸ፤

18. እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከፋራንም ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ በመምጣት፣ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገቡ። ንጉሡም ለሃዳድ ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም አዘዘለት።

19. ፈርዖንም ሃዳድን እጅግ ወደደው፤ ስለዚህም ከሚስቱ ከንግሥት ጣፍኔስ እኅት ጋር አጋባው።

20. የጣፍኔስም እኅት ጌንባት የተባለውን ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስ በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም ከፈርዖን ልጆች ጋር አደገ።

21. ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር ማንቀላፋቱን፣ የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብም መሞቱን ሰማ። ሃዳድም ፈርዖንን፣ “ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ” አለው።

22. ፈርዖንም፣ “እዚህ ምን ጐደለብህና ነው ወደ አገርህ ለመግባት የፈለግኸው?” ሲል ጠየቀው።ሃዳድም፣ “ምንም የጐደለብኝ የለም፣ ብቻ እንድሄድ ፍቀድልኝ” አለ።

23. እግዚአብሔርም ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ኰብልሎ የነበረውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ሌላ ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው፤

24. ዳዊት የሱባን ኀይል በደመሰሰ ጊዜ፣ ሬዞን ሰዎቹን በዙሪያው አሰባስቦ የወንበዴ አለቃ ሆነ፤ ሰዎቹም ወደ ደማስቆ ሄደው ተቀመጡ፤ በዚያም አነገሡት።

25. ሃዳድ ካስከተለበት ችግር ሌላ ሬዞን በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ሌላው የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ ሬዞን ሶርያን ገዛ፤ እስራኤልንም ይጠላ ነበር።

ኢዮርብዓም በሰሎሞን ላይ ዐመፀ

26. እንዲሁም ከሰሎሞን ሹማምት አንዱ የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እርሱም ከጸሬዳ የመጣ ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ እናቱ ጽሩዓ የተባለች መበለት ነበረች።

27. በንጉሡ ላይ ያመፀበትም ምክንያት እንዲህ ነው፤ ሰሎሞን ድጋፍ የሚሆኑ እርከኖች በመሥራት የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ይጠግን ነበር።

28. ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ሰሎሞንም ወጣቱ ሥራውን እንዴት በሚገባ እንደሚያከናውን ባየ ጊዜ፣ በዮሴፍ ነገድ ለሚሠራው የጒልበት ሥራ ሁሉ ኀላፊ አደረገው።

29. በዚያ ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ የሴሎው ነቢይ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ መጐናጸፊያ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱ ብቻቸውን ሳሉ፣

30. አኪያ የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ ይዞ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቀደደው።

31. ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ መንግሥቱን ከሰሎሞን እጅ እቀዳለሁ፤ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጣለሁ፤

32. ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንድ ነገድ ይቀርለታል፤

33. ይህን የማደርገውም እኔን ትተው የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፣ የሞዓብን አምላክ ካሞሽን፣ የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ስላመለኩ እንዲሁም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ስላልሄዱ በፊቴ ትክክለኛውን ነገር ስላላደረጉ፣ ሥርዐቴንና ሕጌን ስላልጠበቁ ነው።

34. “ ‘ይሁን እንጂ መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድበትም፤ ስለ መረጥሁት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ስለ ጠበቀው ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንዲገዛ አድርጌዋለሁ።

35. መንግሥትን ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፤ ለአንተም ዐሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ።

36. ስሜ እንዲኖርባት በመረጥኋት በዚያች በኢየሩሳሌም ከተማ ለባሪያዬ ለዳዊት ምንጊዜም በፊቴ መብራት እንዲኖረው፣ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጣለሁ።

37. አንተን ግን እኔ እወስድሃለሁ፤ ልብህ በወደደው ሁሉ ላይ ትነግሣለህ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ትሆናለህ።

38. ባሪያዬ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን በመጠበቅ ትክክል የሆነውን ነገር በፊቴ ብታደርግ፣ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት እንዳጸናሁ፣ ለአንተም አጸናልሃለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጣለሁ።

39. ከዚህ የተነሣም የዳዊትን ቤት አዋርዳለሁ፤ ነገር ግን ለዘላለም አይደለም።’ ”

40. ሰሎሞን ኢዮርብዓምን ለመግደል ፈለገ፤ ኢዮርብዓም ግን ወደ ግብፅ ሸሸ፤ ወደ ንጉሡ ወደ ሺሻቅ ሄዶ፣ ሰሎሞን እስኪሞት ድረስ በዚያው ተቀመጠ።

የሰሎሞን መሞት

41. የቀረው በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ የሠራውም ሁሉ፣ ጥበቡም በሰሎሞን የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎ የለምን?

42. ሰሎሞን በመላው እስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም የነገሠው አርባ ዓመት ነው።

43. ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።